እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዕርገት

ዕርገት

6e100b693083fe7b237779ffd809d8b7XL

ንባባት፡- ዕብ 1፡ 1-14፣ 1ጴጥ 3፡18-22፣ ሐሥ 1፡ 1-11

መዝሙር፡- ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ (መዝ 46፡5-6)

ወንጌል፡- ማር 16፡14-20

ከትንሳኤ በዓል ፵ ቀናት በኋላ የጌታን ዕርገት እናከብራለን፤ ፵ ቀን የአዲስ ነገር መጀመርያ የተቀደሰ ቀን ነው። ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ፵ ቀን አዲስ ነገር ከመወለዱ በፊት ያለ የአዲስ ልደት ምጥ ነው። ጌታ በግልጽ እየተመላለሰ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማወጁ እና የሰው ልጆችን ወደ ብርኀን ከመጥራቱ አስቀድሞ እርሱ ራሱ ለ፵ ቀን በበርሃ በብቸኝነት፣ እርሱ እና አባቱ ብቻ በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት በሚነጋገሩበት መለኮታዊ ኁባሬ ውስጥ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ማቴ 4፡ 1-2)። ፵ ቁጥር በሦስቱም ታላላቅ ሃይማኖቶች ውስጥ ማለትም በአይሁድ፣ በክርስትና እና በእስልምና የተቀደሰ ነገርን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሎ እንመለከተዋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጉልህ ከምናገኘው የአይሁድ እና የክርስትና የ ፵ ቀን ኝዛቤ ባሻገር በእስልምና አስተምሕሮ አዳም በሕይወት ዘመኑ ለ ፵  ጊዜያት ያህል ወደ መካ እንደተመላለሰ ይነገራል። በሀገራችን የክርስትና እምነት ከአይሁድ በወረስነው እምነት መሰረት ወንድ ልጅ በተወለደ በ ፵ኛው ቀን ጥምቀት ይቀበላል፤ ይህም ነፍስ የማወቅ ምልዓት በ ፵ኛው ቀን ይፈጸማል ከሚል እምነት የሚነሳ ነው። ስለዚህ የዕርገት በዓል ከትንሳኤ በኋላ በ ፵ኛው ቀን መዋሉ በአንድ በኩል የመዳን ታሪክ ምልዓት እና ፍጻሜ መከናወኑን በሌላ በኩል አዲስ ሕይወት ሊጀመር ቀኑ በደጅ መሆነን የሚያመላክት ቁም ነገር ነው።

ከጌታ ትንሳኤ በኋላ ፵ ቀን ቆጥረን የዕርገትን በዓል ስናከብር የመዳን ታሪካችንን ፍጻሜ እና የስብከተ ወንጌል ተልዕኳችንን ጅማሬ በመጠባበቅ ነው። ዕርገት በተፈጸመ እውነታ ኃይል እየተመራን በተስፋ እና በእምነት ወደሚታይ ክብር በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን የምንጓዝበት ሕይወት የመጀመርያው እርምጃ ነው። በመሆኑም ጌታ ለሐዋርያቱ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡19-20) ብሎ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሲሰጣቸው እንመለከታለን፤ ነገር ግን ይህ ሐዋርያዊ ተልዕኮ በሰው ልጆች ኃይል እና ፈቃድ የሚከናወን ሳይሆን ይልቁንም መለኮታዊ ተልዕኮ እንደ መሆኑ መጠን መለኮታዊ ምሪት ያስፈልገዋል። በመሆኑም ጌታ ይህንን ተልዕኮ ከሰጣቸው በኋላ ሌላ ወሳኝ ቁም ነገር ሲነግራቸው እንመለከታለን፤ ይኸውም “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” (ሉቃ 24፡49) የሚለው የጌታ ትዕዛዝ ነው። የስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ጀማሪ፣ መሪ እና ፈጻሚ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ነው።

መንፈስ ቅዱስ ያልጀመረው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተዛባ ብርኀን እንዳገኘው ተክል (Etiolated plant) ዕድገቱ ፈጣን ቢመስልም ሥር ስድዶ መሬት መያዝ የማይችል፣ ልፍስፍስ፣ ቀለሙም የወየበ መሆኑ የማይቀር ነው። መንፈስ ቅዱስ ያላነሳሳው፣ ያልመራው እና ፍጻሜ ያልሆነለት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት “ሰው” ራሱን በእግዚአብሔር የክብር ሥፍራ የሚሾምበትን ዘመናዊ ጣኦት አምልኮ ማስከተሉ የአደባባይ ምሥጢር ነው።

ይህንን የተረዳው የአይሁድ ሸንጎ አባል እና የተከበረው የሕግ መምህር ገማልያል ሐዋርያት በኢየሱስ ስም የሚያደርጉትን ስብከተ ወንጌል እንዲያቆሙ በአይሁድ ሸንጎ በተከሰሱ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ በሚመራ አገልግሎት እና በሰው ፈቃድ በሚመራ አገልግሎት መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚገባ እያሳሰበ እንዲህ ይላል “ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ።  አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ” (ሐሥ 5፡34-39)።

የዕርገት በዓል ከርድዕተ መንፈስ ቅዱስ፣ ከበዓለ አምሳ ፲ ቀናት ቀደም ብሎ መከበሩ በቤተ ክርስትያናችን የምናደርገውን የዘጠኝ ቀን (*የኖቬና) ጸሎት መንፈሳዊ ልምምድ ያስገነዝበናል። የኖቬና ጸሎት የእግዚአብሔርን መገለጥ በእምነት የምንጠባበቅበት የጸጋ ጊዜ ነው፤ በመሆኑም ሐዋርያት በሮቹን ዘግተው ነገር ግን በእምነት የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ይጠባበቁ እንደነበር ማስተዋል እንችላለን። ሐዋርያት የተዘጉትን በሮች ከፍተው ከመውጣታቸው አስቀድሞ ጌታ መንፈስ ቅዱስ የልባቸውን እና የአእምሮአቸውን በር ከፍቶ ነበር፤ እርሱ በሰጣቸው ኃይል የተዘጉትን በሮች ከፍተው እንደወጡ እና ብዙዎችን ወደ ጌታ እንዳመጡ የሐዋርያት ሥራ በስፋት ይተርካል። ዛሬ የዕርገትን በዓል ስናከብር በአንድ በኩል የመዳን ታሪካችንን ፍጻሜ የምሥጋና በዓል በሌላ በኩል ደግሞ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ባለን የክህነት፣ የነብይነት እና የንጉሥነት ተልዕኮ እስከ ምድር ዳርቻ ለሚጠበቀው ምሥክርነታችን ሁሉ የምሥክርነታችን እውነተኛነት ምሥክር የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ መምጣት የምንጠባበቅበት የተስፋ በዓል እናከብራለን። በመሆኑም እስከ ርድዕተ መንፈስ ቅዱስ ያሉትን ቀናት በእምነት የመንፈስ ቅዱስን መምጣት እየተጠባበቅን እንድንመላለስ ተጋብዘናል።

ጸሎት ወደ መንፈስ ቅዱስ

መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና!  የምእመናኖችህን ልብ ሙላ ፤ የፍቅርህን እሳት በውስጣቸን አንድድ ፤ የእውተኛነት ምንጭ የሆነህ መንፈስ ቅዱስ ሆይ በልባችን ውስጥ ግባ ፤ ሕዝቦችህ ትሕትና በተሞላበት ሃይማኖት ደስ እንዲያሰኙ ብርሃንህን አድላቸው።

አሜን!

ሴሞ

 

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት