እምነት (ክፍል ፯)
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Sunday, 17 July 2022 09:37
- Written by Super User
- Hits: 1097
- 17 Jul
“በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ባልፍ...”
እምነት (ክፍል ፯)
ቅዱስ ጳውሎስ “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” (2ቆሮ 5፡7) እያለ የክርስትያናዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ምን እንደሆነ ያሳየናል፤ ነገር ግን ከዚህ ባሻገር በእምነት እንጂ በማየት እንመላለስም የሚለው ሐሳብ ስለ እምነት ብርኀን እና ስለ እምነት ጨለማ እንድናስብ ያስገድደናል። ምንም እንኳን በሕይወታችን ታላላቅ ነገሮች የተከናወኑ ቢሆንም ቅሉ፤ የእምነት ጨለማ በአማኝ ሕይወት ውስጥ ወደ ጎን የሚችል ተራ ነገር አይደለም፤ ይልቁንም በእምነት ጨለማ ውስጥ ማለፍ የእምነት መንገድ አንዱ የዕድገት ጎዳና ነው፤ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” (መዝ 23) እያለ የእምነት ጉዞ በሞት ጥላ ጨለማ ውስጥ ማለፍን የሚያጠቃልል ቁም ነገር ያለበት ጉዞ መሆኑን እንድንመለከት ዕድል ይሰጠናል።
ወደ አዲስ ኪዳን ተመልሰን የጌታን የጌቴሴማኒ ጸሎት ስናስተውል ይህ የእምነት ጨለማ ፍንትው ብሎ ይታያል፤ ኢየሱስ በዚህ ጸሎት “አባት ሆይ ብትፍቅድስ ይህቺ ጸዋ ከእኔ ትለፍ” እያለ የሚያቀርበው ጸሎት የገባበትን ጥልቅ የሞት ጣር የሚያሳይ ሲሆን “ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን” የሚለው የጸሎቱ ሁለተኛ ክፍል ተዓዝዞ ያለበትን የእምነትን ብርኀን የሚያስቃኘን ቁም ነገር ነው። እያንዳንዱ አማኝ በእምነት ጨለማ እና በእምነት ብርኅን መካከል በማየት ሳይሆን በእምነት እንዲመላለስ ተጠርቷል። በእነዚህ በሁለቱ የእምነት ጨለማ ሸለቆዎች ውስጥ ማለፍ የእያንዳንዱ ክርስትያን የእምነት ጉዞ እውነታ ነው።
የዚህ የእምነት ጨለማ ጊዜ እግዚአብሔር መኖሩ እና እኔን ማሰቡ በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባበት ወቅት ነው። የነስፍ ጸሐይ የሚጨልምበት እና ብርኀን የማይታሰብበት፣ በጥልቅ ሸለቆ ውስጥ የመመላለስ ዘመን ነው። በዚህም ወደ እግዚአብሔር መመልከት፣ ወደ እርሱ ለመመለስ መሞከር የሚታሰብ አይደለም፤ ይልቁንም እርሱ የሌለበት ፍጹም ጨለማ እና ፊቱ የተሸፈነበት ጊዜ በመሆኑ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ የሚለው ሐሳብ ከቃላት የዘለለ ተግባራዊ ትርጓሜ የሌለው ተራ ሐሳብ ይሆናል። ዳዊት ይህንን የእምነት ጨለማ ጊዜ ስለቀመሰ እንዲህ እያለ የነፍሱን ጨለማ በአምላኩ ፊት ያቀርባል፡-
“ አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ እስከ መቼ በነፍሴ እመካከራለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ሁልጊዜ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይጓደዳል? አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፤ ጠላቴ አሸነፍሁት እንዳይል፥ የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ። እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በመድኃኒትህ ደስ ይለዋል። የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ” (መዝ 13፡1-6)።
በክርስትያናዊ ጉዟችን በቤተ ክርስትያን ምክር እና በበጎ ፈቃዳችን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብለን የምናደርጋቸው ተግባራት እንዳሉ ሁሉ (ለምሳሌ ጾም፣ ራስን መግራት፣ ምጽዋት ወ.ዘ.ተ.) በመለኮታዊ ፈቃድ የምናልፍባቸው የጨለማ ጊዜያት መኖራቸውንም ማስተዋል ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ እንደወሰደው እንዲሁ እያንዳንዳችንን ደግሞ ወደዚህ “ጨለማ” ስፍራ ያመጣናል፤ ይህ ለሰው ልጅ ዐይን “ጨለማ” የምንለው የእምነት ጉዞ በእርግጥ መለኮታዊ ብርኀን ነው፤ ነገር ግን መለኮታዊ ብርኀንን ለማየት ሰብዓዊ ዐይኖች ለዚህ ብርኀን እስኪበቁ ድረስ በጨለማ ውስጥ ዕይታቸው ለመለኮታዊ ብርኀን እንዲስማማ ተደርጎ መሞረድ አለበት፤ ወደ መለኮታዊ ብርኀን ከመግባታችን በፊት ብርኀን እንዳያሳውረን መንፈስ ቅዱስ ጨለማ በሚመስል እና እግዚአብሔር ፊቱን የሰወረበት በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ዐይኖቻችንን ለመለኮታዊ ብርኀን እየኳለ ያዘጋጀናል።
ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ውስጥ አጥርቶ ስለመመልከት ሲናገር “ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ” (ራዕ 3፡18) እያለ በእሳት በኩል ማለፍ፣ ዕርቃንን በክብር ነጭ ልብስ የመሸፈን፣ አጥርቶ ለማየት ዐይኖችን መኳል እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ቅዱስ ዳዊት በበኩሉ በእምነት ጉዞው የገጠመውን የእግዚአብሔር ዝምታ በሚመለከት “በሞት ጥላ መካከል እንኳን ባልፍ እንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህ እና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል” (መዝ 23፡4) እያለ በጨለማ ስፍራ ሆኖ አምላኩን በመተማመን ይዘምራል።
በዚህ የጨለማ ስፍራ ተስፋ ያደረግንበት ነገር እና የተደገፍንበት የሕይወት ምሶሶ ሁሉ በእሳት ይፈተናል (1 ቆሮ 3፡13-15)፤ በሕይወታችን እግዚአብሔር ሁለተኛ የሆነበት ስፍራ ሁሉ በግልጽ ብርኀን እስኪወረስ ድረስ በጨለማ ውስጥ እያለፈ ወደሚያስደንቅ ብርኀን ይወጣ ዘንድ፣ ለእግዚአብሔር ያልተገዛ የእምነት ሕይወት ክፍል በሰማይ እና በምድር፣ ከምድርም በታች ጉልበት ሁሉ ለሚሰግድለት ለእርሱ እስኪንበረከክ ድረስ ነፍስ የእግዚአብሔር ለዛ ይጠፋባታል። ይህም ነፍስ ከታሰረችበት እና የሙጥኝ ብላ ከያዘችው ነገር ሁሉ እስክትላቀቅ ድረስ የሚዘልቅ የንስሐ ጊዜ ነው። በዚህ የንስሐ ጊዜ ነፍስ ከጥልቅ የእምነት ሸለቆ ውስጥ ሆና አምላኳን በመፈለግ እና በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ እና በፍጹም ኃይል እግዚአብሔርን ማፍቀር ትማራለች። ቅዱስ ዳዊት ይህንን የነፍስ የንስሐ እና ፍጹም በእግዚአብሔር የመታመን ጉዞ በመዝሙሩ እንዲህ እያለ ይገልጸዋል፡-
“ አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ። አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፤ ጆሮህ የልመናዬን ቃል የሚያደምጥ ይሁን። አቤቱ፥ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና። አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች። ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች። ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና...” (መዝ 130፡1-7)።
እዚህ ላይ በጣም አስፈላጊውና ልናስተውለው የሚገባን ቁም ነገር ዳዊት ልቡን በአምላኩ ላይ ማድረጉን እና በእምነት ራሱን በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ መጣሉን ነው። ይዘህ ማዳን፣ ጠብቀህ ማትረፍ የማትችለውን ነገር ተሸክመህ እስከ መቼ ታነክሳለህ? ተሸክመን የምንዞረው ጭንቀት እኛ ራሳችን የምንፈውሰው ቁም ነገር አይደለም። ይህ የእምነት የጨለማ ጉዞ በሕይወታችን ለራሳችን ራሳችን መድኃኔዓለም የሆንንበትን ነገር ሁሉ ለመድኃኔዓለም አሳልፈን መስጠት የምንማርበት እና የሰው ልጅ የጉዞ ጥግ የት ድረስ እንደሆነ የምንማርበት ወቅት ነው። በመሆኑም የእምነት ጨለማ ራስን በእግዚአብሔር ሕልውና ውስጥ የማድረግ ጥሪ ነው። ነገር ግን በማይታይ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ቆሞ የማታይ ነገር ላይ ራስን መጣል እንደሚወራው ቀላል ነገር አይደለም።
በማይታይ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መራመድ እና በዚህ ጉዞ መካከልበስቃይ መካከል እግዚአብሔር የሚሰጠውን ማጽናናት ለማጣጣም መሞከር ደም እንባ የሚያስለቅስ የሕይወት ጉዞ ሊሆን ይችላል። ቅዱስ ዳዊት ይህንን የጨለማ ጉዞ በሚመለከት ሲዘምር “ አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ። ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ። በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው? በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ” (መዝ 6፡1-6) እያለ የነፍሱን ጥልቅ መቃተት በአምላኩ ፊት እያፈሰሰ መጽናናትን ተስፋ ያደርጋል።
ቅዱስ ዮሐንስ ዘ መስቀል “የነፍስ ጨለማ ሌሊት” (The Dark Night of the Soul) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው በእሥር ላይ በነበረበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ እንዴት ባለ ጨለማ ውስጥ እንዳሳለፈው ሲናገር “ማንም ሳያስተውለኝ ወጣሁ” ይላል። ነገር ግን “ማንም ሳያስተውለኝ ወጣሁ!” ማለት ምን ማለት ነው?
ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል በዚህ “ማንም ሳያስተውለኝ ወጣሁ!” በሚለው ሐሳብ ውስጥ ግለሰቡ ከራሱ ሰንሰለት ነጻ እየወጣ፣ ከራሱ ማንነት እየዳነ እንደሆነ ይናገራል። ይኸውም ሰው እግዚአብሔርን የመረዳት፣ እግዚአብሔርን የመውደድ እና እግዚአብሔርን የመፈለግ የቀድሞ መንገዶቹን ወደ ጎን በመተው መንፈስ ቅዱስ በሚያስተምረው አዲስ መንገድ እግዚአብሔርን ማወቅ፣ መውደድ እና በሁሉ ነገር እግዚአብሔርን መፈለግ ይለማመዳል። እነዚያ የቀድሞ መንገዶች ውስን እና ያልበሰሉ፣ በሳት ያልተፈተኑ እና ለዘለቄታው የማያስኬዱ ነበሩ።
ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል ይህንን የነፍስ የጨለማ ሌሊት “መልካም ዕድል ሆይ!” እያለ ይጠራዋል። ይህም ማለት የጨለማው የነፍስ ሌሊት የእግዚአብሔር ታላቅ የጸጋ ሥጦታ ነው ማለት ነው። በፍጥረት መጀመርያ የእግዚአብሔር ቃል እስኪነገር ድረስ በምድር ላይ ጨለማ ሰፍፎ እንደነበረ (ዘፍ 1፡2) እንዲሁ ነፍስ በእግዚአብሔር መለኮታዊ የሕይወት ቃል የተፈጠረችበትን ዓላማ እስክትመስል ድረስ በጨለማ መካከል ታልፋለች። ይህ ጨለማ የብርኀን አለመኖር ብቻ ሳይሆን በነፍስ ውስጥ የእግዚአብሔር አርምሞ መገለጥ ጭምር ነው። ነብዩ ኤልያስ በሆሬብ ተራራ ተሸሽጎ በነበረበት ወቅት የእግዚአብሔርን ቃል ከማድመጡ በፊት በሕይወቱ ይህንኑ የእግዚአብሔርን ዝምታ ማድመጥ ያስፈልገው ነበር!
“እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ” (1ነገ 19፡11-14)።
የእግዚአብሔር አርምሞ እንደ አዲስ የምንፈጠርበት መለኮታዊ ኃይል ነው፤ በመሆኑም ይህ ኃይል በውስጣችን ሙሉ በሙሉ እስኪቀጣጠል ድረስ እግዚአብሔር በዙርያችን በሚከናወኑት ነገሮች ውስጥ ፍጸም የሌለ እሲመስለን ድረስ ዝምታው ያስገርመናል። ይህ የእግዚአብሔር አርምሞ አእምሮአችንን፣ ፍቅራችንን እና ትውስታችንን ይለውጣል። በዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከወተት ወደ አጥንት” (1ቆሮ 3፡2) እንድናድግ የሚመክረን ቁም ነገር በሕይወታችን እውን እየሆነ ይመጣል። የነፍስ የጨለማው ሌሊት ማንነታችንን አያጠፋም፤ ስብዕናችንን አይጸየፍም፤ ከዚህ ይልቅ በመለኮታዊ ባሕርያትና በነፍስ ውስጣዊ ደስታዎች ያድሰናል።
በዚህ መለኮታዊ እና ምስጢራዊ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ብርሃኑን እና እውነቱን ወደ ነፍሳችን እያፈሰሰ በደብረታቦር በጌታ መገለጥ የታየው የሚያጽናና የታቦር ብርኀን በነፍስ ላይ ይጸልል ዘንድ ነፍስ ወደዚህ ከፍታ ትነጠቃለች። ውሱንነታችን ሥፍራ ሲለቅ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅር ወደ ነፍሳችን ይደርሳል፤ በእርሱ እንረሰርሳለን፣ የጠወለገው ዳግም ሕይወት ይዘራል፣ በመንፈስ ቅዱስ እንነጻለን፣ እንጸናለን እንዲሁም እንበራለን። መለኮታዊ ብርሃን በጨለማ ውስጥ ያበራል። እኛ እንደ ሰው አስተያየት መጠን በሕይወታችን የሚከናወኑትን አፍራሽ ነገሮችን እናስተውላለን፤ በመሆንም እግዚአብሔር እያደረገልን ያለውን አወንታዊ ነገር ከማስተዋል እንዘገያለን። እግዚአብሔር እያደረጋቸው ያሉ አወንታዊ ተግባራት ግን የጸጋ መፍሰስ፣ የእግዚአብሔር ሙላት፣ የጠራ ራዕይ፣ መለኮታዊ ብርሃን በነፍስ ላይ ማድረግ ወ.ዘ.ተ. ናቸው።
በጨለማው የነፍስ ምሽት ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ትክክለኛ ትርጉም ይህንን የእግዚአብሔርን አባታዊ ማጽናናት እና ፍቅር በማሰላሰል ውስጥ የሚስተዋል ቁም ነገር ነው። እግዚአብሔር ምስጢራዊ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነፍስን በመለኮታዊ ነጻነት እየዋጀ ፍጹም ከእርሱ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ ይገራታል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንዴት እንደሚከናወን በውል መረዳት አንችልም ነገር ግን በሕይወታችን አዎንታዊ ነገሮች እየተከሰቱ እንደሆነ እናስተውላለን፤ ይህም ቢሆን ግን እንደ ሌሊትና እንደ ጨለማ ባለ ድንግዝግዝ ውስጥ ይታየናል እንጂ ገና የጠራ ዕይታ ላይ አልደረስንም።
ይህ የጨለማ ጉዞ የነፍስን የትኩረት አቅጣጫ እና ዓላማ የሚለውጥ በመሆኑ ተስፋ ሁሉ ከእኛ የተወሰደ እስኪመስለን ድረስ ነፍስ ጥልቅ ከሆነ አለማወቅ እና ጥርጣሬ ውስጥ በሚወለድ መቃተት አምላኳን ትጣራለች። ይህ ጊዜ የመንጻት ጊዜ ስለሆነ የሚያጽናና መንፈሳዊ ደስታ እምብዛም የሚስተዋልበት ጉዞ አይደለም። ነፍስ ከምድራዊ ሰንሰለቶቿ እየተፈታች በመኮታዊ ነጻነት መመላለስ እንድትችል ተደርጋ ትዘጋጃለች። በዚህ ጨለማ ውስጥ ነፍስ ከራሷ እና ከነገሮች ፍቅር ቀስ በቀስ ነጻ እየወጣች ወደ መለኮታዊ ብርኀን ትቀርባለች።
ይህ ጨለማ ነፍስ የወረደችበት የመንጻት ጥግ ሲሆን በሰውኛ ዕይታ ድቅድቅ ጨለማ የሚመስለው ነገር በርግጥ በሚያስደንቅ መለኮታዊ ብርኀን የተሞላ ነው፤ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው” (መዝ 139፡11-12) እያለ በእምነት ጨለማ መካከል የሚያስደንቅ የእግዚአብሔር ብርኀን እንደሚወርሰን ይመሰክራል።የእግዚአብሔርን ብርኀን ማጣጣም እስክንጀምር ድረስ ነፍስ በጨለማ ውስጥ መሆኗ የሚደንቅ አይደለም።
በዚህ የነፍስ የጨለማ ጊዜ የሚሰማን ስቃይ ከሁለት ምክንያቶች የሚነሳ ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው ምክኒያት ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጸጋ የመቀበል አቅማችን ውሱንነት ነው። በጨለማ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሰው የዐይኖቹ የማየት አቅም ጨለማውን ተለማምዶ የዕይታውን ወሰን በዚያ ላይ ስለተከለ በአንድ ጊዜ ለደማቅ ብርሃን ከተጋለጠ ከብርኀኑ ብሩህነት የተነሳ ለጊዜው ህመም ይሰማዋል። ንጉሥ ዳዊት ስለዚህ መንፈሳዊ ሁናቴ እንዲህ እያለ ይዘምራል “መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ” (መዝ 18፡11)። ንጉሥ ዳዊት በዚህ የመንጻት ሁኔታ ውስጥ ሲያልፍ የነበረውን መንፈሳዊ ልምምድ እንዲህ ካቀረበ በኋላ በሚቀጥለው ቁጥር ላይ እግዚአብሔር በብርኀን እንጂ በጨለማ ውስጥ አይደለም እያለ ጨለማው የእግዚአብሔርን ክብር በምልዓት እስከሚያይ ደረስ ዐይኖቹን የጋረደው ቅርፊት መሆኑን ይመሰክራል። የእግዚአብሔር መገኘት በእውነቱ ብሩህነት ውስጥ ነው፤ ይህንን የእውነት ብሩህነት ለመቀበል የነፍስ ዐይን በመለኮታዊ ብርኀን ጨረር መከፈት ይኖርበታል።
በዚህ የነፍስ የጨለማ ጊዜ የሚሰማን ስቃይ ሁለተኛው ምክኒያት ደግሞ ከመለኮታዊ ብርኀን አንጻር እኛ በጣም ዝቅተኛ ሥፍራ ላይ በመሆናችን ነው። በዚህ በዝቅተኛ ሥፍራ ተመቻችተን ለዘመናት ስለተቀመጥን ከዚህ ዝቅተኛ ሥፍራ የተለየ ሌላ ዓለም ያለ አይመስለንም፤ ስለዚህ ለመንፈስ ቅዱስ ጥሪ እና ለመለኮታዊ ብርኀን ስበት የምንሰጠው ምላሽ በእጅጉ የሳሳ ነው፤ በመሆኑም ይህ ከእግዚአብሔር የሚመጣው የብርኀን እና የእውነት ፍሰት በጣም የሚያሰቃይ ነው። ለዘመናት ከታሰርንበት ሸለቆ ነጻ የሚያወጣን ብርኀን እና እውነት ቀስ በቀስ ሁለንተናችንን እየወረሰ ነፍስ እና ሥጋችንን እስኪዋጅ ድረስ ይህ የመንጻት ሥርዐተ እንደ መንፈስ ቅዱስ በጎ ፈቃድ ለተራዘመ ጊዜ ይቀጥላል።
በጨለማው የነፍስ ምሽት ውስጥ ያለው የጨለማ ስሜት በጣም ጠንካራ ሊሆን ስለሚችል በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያጣን፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን የማይሰማን እና በፍጹም ፊቱን ከእኛ የሰወረ ይመስለናል። የሚራራልን እና የሚያግዘን የለም በሚል ስሜት በፍርሃት እንዋጣለን። ከዚህም የተነሳ ጻዲቁ ኢዮብ “እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ማሩኝ” (ኢዮብ 19፡21) እያለ ሲጸልይ እንመለከተዋለን። ነገር ግን የእግዚአብሔር እጅ የሚፈውስ እና የዋህ ነው፤ የእግዚአብሔር እጅ በማንም ሰው ሕይወትና ጸሎት ላይ አይጨክነንም፤ ቀንበሩን በማንም ሰው ጫንቃ ላይ አያከብድም፤ እየገራ ያሳድገናል እንጂ ኃጢያታችንን በሚዛን እየሰፈረ በዋጋ ተምኖ አይቀጣንም። ይልቁንም የእርሱ ዓላማ የተፈጠርንበትን ታላቅ ሞገስን በምልዓት እንድንጎናጸፍ ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህን የሚያደርገው በእግዚአብሔር የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖረን ነው። በእምነት ጨለማ ሸለቆ ውስጥ የማለፋችን መሰረታዊ ቁም ነገር ለመለኮታዊ ብርኀን በተኳሉ ዐይኖች “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ እንበረታ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሰን እንሞላ ዘንድ ነው። እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ሴሞ