እምነት ክፍል ፭
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Monday, 27 June 2022 14:38
- Written by Super User
- Hits: 954
- 27 Jun
በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር የሚሰራ እምነት
በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር የሚሰራ እምነት (ገላ 5፡6) የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ እንደመሆኑ መጠን ከዚሁ ቁም ነገር ጋር የተያያዙትን ሁለቱን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች መመልከቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት ያለውን ተልዕኮ የበለጠ ለመረዳት ያግዘናል። እምነት እግዚአብሔርን መፍራት እና እግዚአብሔርን በልባችን መንበረ ታቦት ለቤተ መቅደስነታችን በሚመጥን ክብር መጠበቅ የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን መፍራት እና ልብን በንጽህና መጠበቅ በእምነት ብቻ የሚደረስባቸው ቁም ነገሮች ሳይሆኑ ይልቁንም የማስተዋል እና የዕውቀት መንፈስ የሚጠይቁ የሕይወት ውሳኔዎች ናቸው። ማስተዋል እና ዕውቀት ባልተከፋፈለ ልብ ለአንድ ጌታ ብቻ እንድንገዛ ያስችለናል። ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ስለዚሁ ሲመሰክር “እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” (ዮሐ 8፡32) ይላል። ወደ ነጻነት የሚያወጣን እውነት የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው፤ ይህም በማስተዋል እና በዕውቀት መንፈስ የተቀበልነው የጸጋ ሥጦታ በመሆኑ ከእያንዳንዱ ግለሰብ ልብ ሥር እውነትን የሚጠማ፣ ጽድቅን የሚፈልግ የነፍስ መቃተት አለ።
የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች፡- ማስተዋል እና ዕውቀት
በእምነት አማካይነት ወደ እውነት ምሥጢር እንቀርባለን፤ እውነት እግዚአብሔር ነፍሳችንን የዳሰሰበት የመጀመርያው መገለጥ ነው። ይህም መገለጥ በመጨረሻ በእግዚአብሔር መንግሥት እርሱን ፊት ለፊት በምናይበት ክብር ፍጻሜውን ያገኛል። በምሥጢረ ጥምቀት በተቀበልነው የልጅነት ጸጋ አማካይነት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ አንደበት እግዚአብሔር አብን “አባ አባት” ብለን እየጠራን ወደዚህ ፍጻሜ በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር በጉዞ ላይ ነን። የዚህ ጉዞ መሪ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት ነው (ገላ 5፡6)።
ነገር ግን ይህ እምነት እርዳታ ያስፈልገዋል፤ በእምነት እንድንጸና እና እንድንጽናና የሚረዱን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ያስፈልጉናል፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ” (ኤፌ 3፡16) እያለ የእምነት ሕይወት ከመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች አንጻር የሚጸና መሆኑን ይናገራል። የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ለነፍሳችን ድህነት እና ለተፈጠርንበት ዓላማ ምልዓት የሚጠቅሙን የእግዚአብሔር አባታዊ ምክሮች ናቸው። ስለዚህም ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርኀን ነው” (መዝ 119፡105) እያለ በእምነት ጉዞው የሚመክረውን የእግዚአብሔርን ሕግ ያወድሳል። ይህ ለመንገድ የሚሆን እና እግሮቻችን እንዳይደናቀፉ የሚጠብቅ ብርኀን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው፤ በዚህም በእምነት ጉዟችን በማየት ሳይሆን በማስተዋል፣ በስሜት ሳይሆን በዕውቀት እንመላለስ ዘንድ የሕይወት ግብረገብ የሚያስተምረን በምሥጢረ ጥምቀት የተቀበልነው መለኮታዊ ምክር በነፍሳችን ውስጥ አለን።
ነገር ግን ይህ በነፍሳችን ውስጥ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ጸጋ በየዕለቱ በምናደርጋቸው የሕይወት ምርጫዎች አማካይነት በውስጣችን እያበበ እና እያፈራ ያድጋል። ጸጋ በነጻ ፈቃድ በሚደረግ ውሳኔ በሥራ እየተገለጠ የሚያድግ የእግዚአብሔር ሥጦታ እንጂ ያለ እኔ ነጻ ፈቃድ እግዚአብሔር ለፈለገው ነገር እኔን የሚያስገድድበት ኃይል አይደለም፤ በመሰረቱ እግዚአብሔር ከእኔ ነጻ ፈቃድ ነጻነት በላይ የሚፈልገው ነገር የለውም። ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ነጻነታችን ክብር እጅግ የሆነውን የእርሱን መለኮታዊ ሕይወት ዛሬ እና አሁን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እያስታወሰን “ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” (2ቆሮ 4፡7) ይላል።
የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ተልዕኮ እያንዳንዳችን ለእግዚአብሔር ሐሳብ የተመቸን፣ በእኛ ላይ ላለው የፍቅር ዓላማ የተዘጋጀን፣ መለኮታዊውን ዘር ተቀብለን መልካም ፍሬ እናፈራ ዘንድ የተስማማ ለም አፈር እንሆን ዘንድ ማበጃጀት ነው። በዚህም ወደ ቅድስት ሥላሴ ኅብረት እየናፈቀ በውስጣችን ከሚቃትተው የእግዚአብሔር መንፈስ ጋር በሰመረ ተግባቦት የሕይወታችንን ዓላማ ሁሉ “ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ” (ሉቃ 5፡5) በሚል እምነት እንድናደርግ የሚያስችሉን ስጦታዎች ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ መመላለስ ለጥቂቶች የተሰጠ የቅድስና አክሊል ሳይሆን ይልቁንም በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በተወለድን ጊዜ ለእያንዳንዳችን የተሰጠን የጸጋ ሕይወት ነው። በመሰረቱ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ የተወለደ (ዮሐ 3) በዚህ በተወለደበት የእግዚአብሔር መንፈስ ይኖር ዘንድ ባሕርያዊ ግብሩ ነው፤ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና” (ሮሜ 8፡14)።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መገለጡ እኛን ከኃጢአት ቀንበር ለማዳን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም አስቀድሞ ከዘላለም ጀምሮ በቅድስት ስላሴ ልብ ውስጥ ወደ ታሰብንበት፣ ወደታወቅንበት እና ወደ ተወደድንበት የልጅነት መልክ ይመልሰን ዘንድ ነው። በመሆኑም በዚህ መልክ እንገለጥ ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት አዲስ ፍጥረት በመሆናችን በሰማይ እና በምድር መካከል፣ በተፈጸመ ድኅነት እና በሚፈጸም ተስፋ መካከል፣ በተከፈለ ዕዳ እና በምንቀበለው የክብር ነጻነት መካከል እንገኛለን። ስለዚህም ሥራችን እና ሐሳባችን ሁሉ በዚህ ምድር በሚታዩት ነገሮች ብቻ ፍጻሜውን የሚያደርግ ሳይሆን ይልቁንም ከዘላለማዊ ሕይወት ጥሪያችን ጋር ግንኙነት ያለው ቁም ነገር ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ጥሪያችንን እያስታወሰን “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ 12፡2) እያለ ይመክራል። በዚህ ዓለም መኖር እና ይህን ዓለም መምሰል ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ እንድንመስለው የተሰጠን ዘላለማዊ መልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱ በዚህ ዓለም ነበር ነገር ግን ከዚህ ዓለም አልነበረም (ዮሐ 8፡23)፤ ስለዚህ በመጨረሻው ሰዓት በጌተ ሰማኒ በጸሎት ላይ ሳለ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” (ዮሐ 17፡22) እያለ እያንዳንዳችንን በጸሎት ወደ አባቱ ሲያቀርበን እንመለከታለን። የመንፈሳዊ ሕይወታችን ሁሉ ችግር እግዚአብሔር ስለ እኛ ባለው እና እኛ ስለራሳችን ባለን ግንዛቤ መካከል ያለው ልዩነት ነው! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ግንዛቤ እንድናስተካክል በሚያስችለን መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ የብስለት ደረጃ ላይ መድረስ የምንችልበትን የሕይወት መንገድ እያስተዋወቀን “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” (ቆላ 3፡21) በማለት የዕይታ ለውጥ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የራዕይ ለውጥ እንድናደርግ ይጋብዘናል። እምነት በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ ያለን ድርሻ በመሆኑ ራሳችንን እና ፍጥረትን በሙሉ በእግዚአብሔር ዐይኖች እየተመለከቱ ከመለኮታዊ ሐሳብ የተነሳ ትርጓሜያቸውን ማጤን እንድንችል ዕድል ይሰጠናል።
የማስተዋል እና የዕውቀት መንፈስ እምነታችንን ተራ መረዳት ወይም ዕውቀት የሚያደርጉ ሥጦታዎች ሳይሆኑ ይልቁንም እምነታችን ከባሕርያዊ ነገር ባሻገር ያለውን መለኮታዊ ጥበብ ማስተዋል የምንችልባቸው ብርኀናት ናቸው። እምነታችንን በተግባር የምንገልጽበት ጥበብ በእነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች አማካይነት በነፍሳችን ላይ ፈስሷል፤ በዚህም እምነታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር እንደሚሰራ እምነት (ገላ 5፡6) በተግባር እየተገለጠ ያድጋል። ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ ስለ መንፈሳዊ ሕይወታችን ኃላፊነቱን ይወስዳል ማለት ነው፤ በዚህም መሰረት ይመራል፣ ይለያል፣ ያጸናል፣ ያጽናናል፣ ያስጨክናል፣ ራዕይ ይሰጣል፣ ለእግዚአብሔር ዓላማ የተመቸን አድርጎ ይቀርጸናል። እርሱ ጌታን ወደ በረሃ እንደወሰደው እና ፈተናን ሁሉ ታግሶ ይጸና ዘንድ፣ ክፉንም በእግዚአብሔር ቃል እየተቃወመ እውነት እና ጽድቅን ይገልጥ ዘንድ እንዳደረገው እንዲሁ እያንዳንዳችንን በተመሳሳይ መልኩ ያዘጋጀናል።
በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረውን ሕይወት በእያንዳንዳችን ውስጥ ደግሞ ይኖር ዘንድ ለዚህ የክብር ቤተ መቅደስነት የምንቀባበት ሜሮን ነው። በዚህም እያንዳንዳችን በተፈጠርንበት ዓላማ እና ለእርሱ በሚመጥን የክብር ሕይወት እንድንኖር መንፈስ ቅዱስ ከዕለት ተዕለት ድግግሞሽ ዑደት ባሻገር ያለውን ሰው ሆኖ የመፈጠር ቁም ነገር በውስጣችን ይቀሰቅሳል።
ሴሞ