እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰንበት ዘሆሳዕና

 

ሰንበት ዘሆሳዕና

ንባባት፡- ዕብ 9፡11-28፤ 1ጴጥ 4፡1-11፤ ሐ.ሥ 28፡11-31፤

ወንጌል፡- ማቴ 21፤1-11

መዝሙር፡- ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ…

ምሥባክ፡- “ ብሩክ ዘይመጽእ ብስመ እግዚአብሔር፥ ባረክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔ እግዚእ አስተርአየ ለነ፥ በእግዚአብሄር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ፤ እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ለእኛም በራልን” (መዝ 117 26-27)

47571218032 ba75b5f758 bሆሳዕና! በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!

የሆሳዕና ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መግባቱን የምናሰላስልበት ሰንበት ነው። ይህ የሆሳዕና ሰንበት የዐቢይ ጾም መደምደሚያ እና የሰሙነ ሕማማት መክፈቻ ሰንበት ነው። አሁን ሙሽራው በደጅ ነው! የሚታረደው በግ፣ አብርሐም ለልጁ ለይስሃቅ የተናገረው እግዚአብሔር የሚያዘጋጅወ፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ምሥክርነት የዓለምን ኃጢአት የሚያጠፋው የእግዚአብሔር በግ እነሆ በደጅ ነው። ይህ ሰንበት የዐቢይ ጾም ጉዟችንን የምንፈትሽበት፣ ጌታን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ መሆናችንን የምንጠይቅበት እና ከራሳችን ጋር የምንተሳሰብበት ሰንበት ነው። ሽልማት ለመቀበል የተገባን በሚያደርግ ተጋድሎ እዚህ የደረስን እንደሆነ ጌታ “አንተ መልካም እና ደግ አገልጋይ” ሲል ምሥጋናውን ይናገራል፤ ምናልባት እንደሚገባን ያልተመላለስን እንደሆነ ግን ጌታ የመጣው በምሕረት በር በኩል በመሆኑ የምሥጢረ ንስሐ ዕድል እንዳለን በማሰብ ያጽናናናል!

አስቀድሞ በትንቢተ ዘካሪያስ 14፡4 “የእግዚአብሔር ቀን” ተብሎ ከተገለጸው ትንቢት ጋር በማያያዝ ወንጌል ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንዴት እንደገባ ይገልጽልናል። ኢየሱስ በተደጋጋሚ የአይሁድን በዓላት ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር። ነገር ግን የዛሬው አገባቡ ከሌላ ጊዜ  የተለየ ነው፤ እርሱ እንደ ቀደሙት ነገሥታት በደብረዘይት ተራራ በኩል አድርጎ በስተምሥራቅ መግባቱ የንጉሥነቱ ምልክት እና መገለጥ ነው። ሕዝቡ ለኢየሱስ ያደረገለት አቀባበል የሚያሳየው ቁምነገር ጌታ በምሥራቁ በር እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ ወደ ከተማይቱ መግባቱ ለእሥራኤላውያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ነው። ይህ የምሥራቁ በር በዕብራይስጥ ቋንቋ ከሚጠራባቸው ስሞች አንዱ “שער הרחמים ሻር ሃርሃሚም” የምሕረት በር የሚል ይገኝበታል። ይህም የእግዚአብሔር ምሕረት እና ክብር ወደ ከተማዋ የሚገባበት በር ለመሆኑ ምሥክር ነው። ነቢዩ ሕዝቄል “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ፤ እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤... የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ” (ሕዝ 43፡1-5) እያለ ይናገራል።  ይህ በር በእሥራኤል ዘንድ “ወርቃማው በር” እየተባለም ይጠራል። ነቢዩ ሕዝቄል በትንቢቱ "የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" (ሕዝ 44:1-2) እያለ የሚናገረው ስለዚሁ በር ነው። እንዲሁም ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 3:2 “መልካም በር” እየተባለ ይጠራል። ወንጌላው ቅዱስ ማቴዎስ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ በብሉይ ኪዳን በትንቢተ ኢሳያስ 62፡11 አዳኝሽ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር ለሰዎች የሚከፍለው ዋጋና ሽልማት አለ ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሩአት” በተመሳሳይም ዘካሪያስ 9፡9 “ጽዮን ሆይ! ደስ ይበልሽ! ኢየሩሳሌም ሆይ በደስታ እልል በይ! እነሆ ንጉሥሽ በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ በድል አድራጊነት ወደ አንቺ ይመጣል” እየተባለ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ይተርክልናል።

 ኢየሱስ በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ የሚለው ሐሳብ የአህያ ውርንጫ ያለውን ትርጉም እንድንጠይቅ ግድ ይለናል። በምሥራቃዊያን ዘንድ አህያ የሰላም ምልክት ነው። ንጉሥ ወደ ከተማ ሲገባ እንደ ሰላም ዘብ እና እንደ ሰላም አለቃ በአህያ ተቀምጦ መግባቱ የተለመደ ነገር ነው። ፈረስ የውጊያ፤ የጦረኝነት፣ የኃይል ምልክት እንደሆነ ሁሉ፤ አህያ የሰላም ምልክት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ለማመልከት በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ኢሳያስ በትንቢቱ ኢየሱስን ሲያስተዋውቀን “ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ 9፡6) እያለ የተናገረው ትንቢት ኢየሱስ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በምሥራቁ በር ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም በመግባቱ የትንቢቱ ፍጻሜ አሁን በግልጽ ይታያል።

በ2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9፡13 ላይ ኢዮሳፋጥ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ የተደረገለት ንጉሣዊ አቀባበል ስንመለከት እሥራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ ልብሳቸውን አውልቀው በመንገድ ላይ በማንጠፍ ነገሥታትን የመቀበል ልምድ እንደነበራቸው መገንዘብ እንችላለን። ኢየሱስም የጽዮን ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ስለገባ የንጉሥ አቀባበል ተደርጎለታል።

በዮሐንስ ራዕይ 7፡9 እንደምናገኘው በሰማያት ወደ እግዚአብሔር ክብር የገቡ ቅዱሳን ሁሉ በእጃቸው ዘንባባ ይዘው እግዚአብሔርን ያመስገኑ ነበር። ዘንባባ ልምላሜው የሚማርክ ተክል ነው፤ ዘንባባ ባለበት ሥፍራ ሁሉ በአብዛኛው ውኃ ስለሚኖር ዘንባባ የመረስረስ፣ የሕይወት፣ የተስፋ ምልክት ነው። በሰማይ የሚገኙ ቅዱሳን የድል ምልክት አድርገው በእጆቻቸው የያዙት ዘንባባ እኛም በዕለተ ሆሳዕና ስንጠቀምበት ኢየሱስ በህማማቱ ድል እንዳደረገ፣ በሞቱ ሞትን እንደሻረ በመመስከር እኛም የድል ተካፋዮች፣ የትንሳኤ ህዝቦች መሆናችን የምንመሰክርበት ነው።እንደ ቤተክርስትያናችን ሥርዐተ አምልኮ “ሆሳዕና” እያልን በቤተክርስትያን ዙርያ ዑደት እናደርጋለን። ምዕመናን ይህንን የተባረከ የሰላም፣ የአሸናፊነትና የተስፋ ምልክት የሆነውን ዘንባባ ወደቤታቸው ይወስዳሉ። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በታላቅ አጀብና በታላቅ ክብር እንደገባ ሁሉ እኛም በታላቅ ደስታ ወደ ቤተክርስትያን እንገባለን።

ዲያቆንና ህዝብ በውጪ ቆመው፣ ካህናት የቤተክርስትያን በር ዘግተው በውስጥ ሆነው በመቀባበል ያዜማሉ። ዲያቆንና ህዝብ በውጪ ሆነው ዲያቆን በመስቀሉ የቤተክርስትያንን በር በማንኳኳት “አርኅው ኆኃተ መኳንንት” (መኳንንት ደጁን ክፈቱ) እያለ ያዜማል። ካህናት ደግሞ በቤተክርስትያን ውስጥ ሆነው “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሰ ስብሀት?” (ይህ የክብር ንጉስ ማነው?) በማለት ይጠይቃሉ። ዲያቆን መልሶ “እግዚአብሔር አምላክ ኃያላን ውእቱ ዝንቱ ንጉሰ ስብሀት አርኅው ኆኃተ መኳንንት” (የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር እርሱ የክብር ንጉስ ነውና መኳንንት በሩን (ደጁን) ክፍቱ) በማለት መልስ ይሰጣል። ይህ ሶስት ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ካህናት የቤተክርስትያኑን በሮች እየከፈቱ “ይባእ ንጉሰ ስብሀት ይባእ አምላክ ምህረት” (የክብር ንጉስ፣ የምህረት አምላክ ይግባ) በማለት በደስታ ያስገቡናል።

ይህ ሁሉ የመዳን ታሪካችን ጉዞ ምሥክርነት ነው። እግዚአብሔር አምላክ በዘመናችን ያደረገልንን መልካም ነገር ሁሉ በሥርዐተ አምልኳችን ውስጥ እንዲህ ባለ ምሥክርነት እና ምሥጋና ምላሽ እንሰጣለን። ሥርዐተ አምልኮ የተኖረ የስብከተ ወንጌል ምሥክርነት ነው። ሥርዐተ አምልኮ እግዚአብሔር አምላክ በታሪካችን ውስት ላከናወነው ነገር ሁሉ በሥጋ እና በነፍስ የሰመረ ኅብረት በሁለንተናችን የምንመሰክርበት አጋጣሚ ነው። ሥርዐተ አምልኮ ያለፈውን ዘመን በመናፈቅ ወደኋላ የምንጎተትበት ልብ ወለድ ሳይሆን ትናንትና፣ ዛሬ፣ እስከ ዘላለም አንድ የሆነወን እና የማይለዋወጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት እና በመንፈስ የምናመልክበት፤ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ሳይምታቱ የሚጋጠሙበት የፍጥረት ሁሉ የምሥጋና በዓል ነው!

ኢየሱስ በሆሳዕና ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ከገባ በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ በግባቱን ወንጌል ይናገራል፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለቤተ መቅደስ ያልተገባ የንግድ ተግባር በሚፈጽሙት ሰዎች ላይ ያደረገውን ነገር ወንጌል ያስነብበናል። ነገር ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚናገረው ዛሬ ቤተ መቅደሱ የእያንዳንዳችን ልብ ነው። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነን። ከእርሱ ጋር በሥጋውንና በደሙ በኩል ባለን ቊርባናዊ ትሥሥር እርሱ በውስጣችን ሕያው ይሆናል። ልባችን የኢየሱስን ሥጋ እና ደም የሚያርፍበት ቤተ መቅደስ በመሆኑ አምላክን በሚያሳዝን የሰው ልጆችን በሚጎዳ ሐሳብ ምርኮኛ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። እነዚህ ነገሮች በልባችን መንበረ ታቦት ለኢየሱስ የሚሆነውን ሥፍራ ይዘው ከሆኑ ዛሬ ልናስወግዳቸው ይገባል፤ የኢየሱስ ቤት ለመሆን የተገነባ ቤተ መቅደስ ሆኖ ይገኝ ዘንድ ዘወትር ልባችንን መጠበቅ እና ለልባችን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ የመንፈሳዊ ሕይወት ልምምድ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ በተለይ በዚህ በህማማት ሳምንት ወደ ህይወታችን፣ ወደ ልባችን ለመግባት በመፈለግ በደጅ ቆሞ ያንኳኳል፤ ይህ ሥርዐተ ቤተክርስትያን ይህንን ሀቅ ያስታውሰናል። ጌታ “እነሆ እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ” (ራዕ 3፡20) እያለ የልባችንን በር ከፍተን እናስገባው ዘንድ፣ በፈቃደኝነት እንቀበለው ዘንድ ይጠብቃል ። ዛሬ ወደ ህይወታችን፣ ተስፋ ወደ ቆረጥንበት ነገራችን፣ ወደ ትዳር ህይወታችን፣ ወደ ቤተሰባችን፣ ወደ ሀገራችን በአጠቃላይ በሁሉም አቅጣጫ አምላክ ይገባ ዘንድ ይጠይቀናል። በንስሐ ወደ እርሱ ተመልሰን ህይወትን ከእርሱ ጋር ሀ ብለን ለመጀመር እድሉ ሰጥቶናል፤ ስለዚህ “ዛሬ ድምጹ ብትሰሙ ልባችሁን እልኸኛ አታድርጉ” (ዕብ 3፡15)።

ኢየሱስን ወደ ህይወታችን ፈቅደን ብናስገባው የዘላለም ህይወት አለን፤ ምክኒያቱም “ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ አገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራዕ 3፡20) ያለው አምላክ የሕይወት እንጀራ ነው! ኢየሱስ ዛሬ በሕዝባችን መካከል፤ በመሰባሰባችን መካከል ለመግባት ይፈልጋል። የዛኤው ዓለም አምላክን ከመካከሉ አስወግዶ ደስተኛ የሆነ ይመስላል። ሰው ኃጢአት የለሆነ ነገር በአደባባይ ትክክለኛ ነገር ነው በማለት ጥብቅና ሲቆም እንመለከታለን። ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ሰዎች ሳይቀሩ በማይረባ ነገር ተጠምደው እናያለን፤ በቃል ኪዳን መሃላ ያሰሩ እንደዘበት መለያየታቸው የጤናማ ሰው ባሕርይ ሆኖ ተቀብለነዋል። ነገር ግን ዛሬ ኢየሱስ በዚህ ሁሉ መካከል እኔ ልግባ፤ ሁሉን ነገር አዲስ አርገው ዘንድ አስገቡኝ፤ ተቀበሉኝ አድምጡኝ እያለ ጥሪውን ያቀርባል። አይሁድ ልብሳቸውን፤ የዛፍ ቅጠሎቻቸውን፤ የአህያ ውርንጫቸውን እንደሰጡት ሁሉ እኛም ያለንን ነገር በሙሉ ለኢየሱስ አሳልፈን በመስጠት እንቀበለው ። እንግዳችን ኢየሱስ ይመጣል፤ በልባችን ደጅ ቆሞ እስከምንከፍትለት እያንኳኳ ይጠብቃል።

የተቀደሰ ሰሙነ ሕማማት ያድርግልን!

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት