እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰሙነ ሕማማት

738d4cfca208fd24c93e01c555c7f6b6 XL

መስቀል

የጌታችን ቅዱስ መስቀል የተፈጠርንበት እና የዳንንበት የእግዚአብሔር ጥበብ፣ ለዘላለማዊ ሕይወት ያለነቀፋ የምንጠበቅበት የመማጸኛ ከተማችን ነው። ስለ ቅዱስ መስቀል ለመናገር ምናልባትም “የሚታየው ነገር ሁሉ ምሥጢር ነው” የሚለውን የራሺያውን የሥነ ጥበብ ሰው የዶስቶቭስኪን ቃላት መዋስ ይጠበቅብን ይሆናል። የመኖራችን እና የሕላዌያችን ቁም ነገር ሁሉ ምሥጢር ነው፤ የተገኘንበት ምንጭ በራሱ ሊደረስበት የማይችል ዘላለማዊነት ውስጥ የተገለጠ ምሥጢር በመሆኑ ወደዚያ ምሥጢር ብርኅን ለመቅረብ የሚቻል አይደለምና እግዚአብሔር አምላክ ለታላቁ ነቢይ ለሙሴ “እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፤ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” (ዘጸ 33፡23) እያለ የምሥጢሩን ጥልቀት ይናገረዋል።

ይህ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሰላም እና አርምሞ የሚደመጥበት እና ይህ ጥልቅ ብርኀን የሚታይበት በር አስፈላጊ ነገር ነው። የሰው ልጅ ክፍጥረት ሁሉ ተለይቶ የዕለት እንጀራውን በማግኘቱ ብቻ ሳይሆን የዕለት እንጀራውን በሚሰጠው አምላክ ላይ ባለው እምነት ሕያው የሚሆን እና የአምላኩን ፊት በማየት በሕይወት የሚኖር ፍጥረት ነው። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረው ከዚህ መልክ የተነሳ ሕያው እንዲሆን ነው እንጂ የራሱ እኔነት ያለበት ሌላ ሕያው የሚያደርገው መልክ የለውም። ይልቁንም የተፈጠረበትን መልክ በመሰለ መጠን የእግዚአብሔር ልጅነቱ እየተገለጠ ወደማይደረስበት የቅድስት ሥላሴ ብርኀናዊ አርምሞ እየቀረበ ይመጣል። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የሕይወት መንገድ በሚመለከት “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ ደግሞ እኔን ምሰሉ” (1ቆሮ 11፡1) እያለ ይመክራል። የሰው ልጅ በእምነት አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ በተኳለ ዐይን የአምላክን ውበት መመልከት እና ማድነቅ ይችል ዘንድ  አዲስ ዕይታ ይቀበላል።

በዚህ እምነት የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወታችን እንዲከናወን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችን ራሱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲከናወን ሆኖ እንደ አዲስ ይታነጻል። እግዚአብሔር ለራሱ መለኮታዊ ፍላጎት በእኛ ሕይወት ውስጥ ሊያከናውን የሚፈልገው ምንም ዓላማ የለውም፤ ይልቁንም በሕይወታችን እግዚአብሔር ሊያከናውነው የሚፈልገው አንድ ዓላማ በኃጢአት ምክኒያት በጠወለገው መልክ ሳይሆን በተፈጠርንበት የእግዚአብሔር ልጅ መልክ ክብር እንድንገለጥ ዘንድ ነው። እርሱ ራሱ ወደዚህ መልክ ይመራን እና እውነተኛ መልካችንን ያሳየን ዘንድ ሰው ሆኖ ተገልጧል! እግዚአብሔር አምላክ ሰው የሆነው ከኃጢአት ብቻ ሊያድነን ሳይሆን የዳነ አዲስ ፍጥረት ምን እንደሚመስል በሰውነት ምልዓት ሊያሳየን ጭምር ነው። እርሱ ከልቡ ዘላለማዊ ፍቅር ፈጥሮናልና ዘወትር ከእኛ ጋር ለመኖር ይመኛል፤ እርሱ ከእኛ ጋር ለመኖር ከመጣበት መውረድ ጋር በማይነጻጸር ክብር ወደ እርሱ ከፍ ሊያደርገን በመስቀል ላይ እርሱ መጀመርያ ከፍ ብሎ ተሰቀለ። ስለዚህም “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” (ዮሐ 12፡32) እያለ በመስቀል ጣር መካከል ሆኖ ቢሆንም ናፍቆቱ ከእኛ ጋር መሆን እንደሆነ በግልጽ እናገራል። በመሆኑም በዚህ ፍቅር የሚያምን ቢኖር ሕይወቱን ሁሉ ለዚህ ፍቅር እንደሚበጅ አድርጎ ያስተካክላል። ለዚህ ፍቅር የሚበጅ ሕይወት ማለት ሌሎች ኢየሱስን የሚገናኙበት መንበረ ታቦት ሆኖ ለመታነጽ በፈጣሪ እና በሕይወት ሰጪ መንፈስ ቅዱስ እጆች ውስጥ ራስን በእምነት አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ ነገር “በመስቀል ምልክት” የተደረገ “እነሆ እኔ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” (ራዕ 21፡5) የሚለው የተስፋ ቃል ፍጻሜ ነው።

1. ቅድመ ዓለም

እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ሲፈጥር በፍጥረት ሁሉ ላይ የተነፈሰው እስትንፋስ በልቡ ከዘላለም ጀምሮ የነበረውን በቃላት ሊነገር የማይችል ፍቅር ነው። እርሱ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ጊዜ የማይሰፈርለት ሆኖ ሳለ በፍቅር ትህትና ከእኛ ጋር ዘመን ሊቆጥር፣ ጊዜ ሊሰፍር ወደደ። በኅላዌው ሊደረስበት የማይችል አዕምሮን ሁሉ የሚያልፍ ሆኖ ሳለ በሚታየው ዓለም ውስጥ በድንበር ሊገደብ፣ እንደ ሰው በተፈጥሮ ሊገለጥ ወደደ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው ይህንን ምሥጢር ሲገልጥልን “ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከሰማያት ስቦ እስከ ሞት አደረሰው” እያለ የፍቅሩን ኃያልነት ያወድሳል።

እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊው ሎጎስ (λόγος) በኩል በመንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ ኃይል ዓለምን እና ሞላዋን ካለመኖር ወደ መኖር ጠርቷታል፤ በዚህ አግባብ ቀድሞ ካልነበረው ጋር በመለኮታዊ ፈቃዱ ቃል በኩል ግንኙነት መስርቷል። እርሱ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ እንደምንመሰክረው “አልቦ እምቅድሜሁ ወአልቦ እምድኅሬሁ፤ ወአልቦ ዘከማሁ፤ ወአልቦ ዘየአምር ዘከመ እፎ ውእቱ፤ ዘውእቱ ህልው እምቅድመ ኲሉ” (ከእርሱ አስቀደሞ የለም፤ ከእርሱ በኋላም የለም፤ እንደ እርሱ ያለ የለም፤ እንዴትም እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ የነበረ ነው)። አሁን ግን ስለእያንዳንዳችን ሲል በታሪካችን ውስጥ ገብቷል፤ ለራሱ ወሰን ባይኖረው እንኳን ስለ ፍቅር ወሰን ያለው ሥጋ ለብሶ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ አስቀድሞ እንመስለው ዘንድ እያንዳንዳችንን ያፈቀረበት ፍቅር “ትስብዕቱ” ነው። የዓለም ኅላዌ ረቂቅ ምሥጢር የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ይህም ፍቅር ራሱን ያለገደብ ሊሰጥ የማይገደበውን እሱነቱን በሰው ልጅ ውኃ ልክ ገድቦ እኛን እስኪመስል ድረስ ራሱን ባዶ ያደረገበት (κένωσις) ፍቅር ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን ፍቅር ሲተረጉምልን “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ 15፡13) እያለ ፍቅሩ ራሱን እስኪሰጥ እኛን እንዲመስል እንዳስገደደው ይናገራል።

ይህ ራስን የመስጠት ፍቅር እንግዳ በሆነ ሁኔታ በመስቀል ላይ ፍጹም ሆኖ የሚታይ እና በጦር ከመከፈቱ አስቀድሞ እርሱ በሰጠን አርአያ እና አምሳል ዘወትር ወደ ፍቅሩ ጥልቀት እንመለከት ዘንድ ፍጹም ሆኖ የተከፈተው ልብ መገለጥ የመስቀል የፍቅር ታሪክ ነው። በዚህ ፍቅር መገለጥ የሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር ምን እንደሆነ እንዲቀምሱ እና እንዲያውቁ ፍቅር በመስቀል ላይ ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ፤ ወደ ላይ እና ወደ ታች ያለከልካይ እርቃኑን ተገልጧል። ይህ በድካም የተገለጠው ፍቅር ከሞት እንኳን የሚበረታ ነው (1ቆሮ 13፣ መኃ 8፡6)።  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበኩሉ ይህንን አዲስ ፍቅር በሚመለከት የገዛን እና የተገዛንበት ዋጋ ምን እንደሆነ ሲናገር “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ” (1ጴጥ 1፡18-20) እያለ ያስታውሰናል።

በእርግጥ ከመጀመርያው አስቀድሞ የሰው ልጅ መገለጥ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ የነበረ ዘላለማዊ ናፍቆት እና ከእኛ ጋር የመኖር ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ግልጽ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ ፍጥረት ራሱ ከመስቀል ምሥጢር ወጪ የሚታሰብ አይደለም። የፍጥረት ሁሉ ትክክለኛ መልክ እና የኅልውና ምሥጢር  በጌታ መስቀል በኩል ካልሆነ በስተቀር ሚዛናዊ የሆነ ትርጓሜ አይገኝለትም። መስቀል የፍጥረት ሁሉ ኅልውና የተነገረበት የመጨረሻው ዓ.ነገር ነው። ከዘላለም ጀምሮ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ተሸሽጎ የነበረው ፍቅር በመስቀሉ በኩል የፍጥረት ሁሉ ኅልውና ምሥጢር መግለጫ ሆኖ ቀርቧል።  መስቀል የፍጥረት ሁሉ ዘላለማዊ ምንነት መፍቻ ቁልፍ ነው፤ በእግዚአብሔር ራስን የመስጠት ፍቅር በኩል ፍጥረት ሁሉ በጎልጎታ በአዲስ ልደት ተገልጧል።

በፍጥረት መገለጥ ውስጥ የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅነት እና የለበሰው ክብር በመስቀሉ በኩል የሚታይ ሆኗል፤ መስቀል ወደ ሕይወት ባለቤት እና ምንጭ እንድንመለከት በር ይከፍትልናል። ከመስቀል ወጪ ፍጥረት በራሱ ምንም ትርጉም ባልኖረው ነበር፤ ፍጥረት ሁሉ ከእግዚአብሔር ልብ ፍቅር የተነሳ ካለመኖር ወደ መኖር እንደመጣ ሁሉ ከወደቀበት ጥልቅ ሊነሳ እና ሊድን ብሎም ወደ ተፈጠረበት ክብር ሊደርስ የሚችለው ከእግዚአብሔር ልብ በሚነሳ እና በመስቀል ምልዓት በሚገለጥ ፍቅር ነው። በዚህ መልኩ የመጀመርያው አዳም ወደራሱ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ወደ ክርስቶስ በተስፋ የሚመለከት ዕድለኛ ፍጥረት ነው።

የፍጥረት ሁሉ ቀመር እና ፍጻሜ የሆነው ወደ ትስብእቱ የሚያመለክተውን የፍጥረትን ሁሉ ምልዓት እና ማንነት በልቡ ጠብቆ የያዘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመርያው አስቀድሞ ዓለምን ሁሉ ወደተፈጠረበት ክብር ሊመራው እና በእርሱም በኩል ፍጻሜውን ያገኝ ዘንድ ከፍ ሊያደርገው ከዘላለማዊ አባቱ የመስቀልን ተልዕኮ በገዛ ፈቃዱ ተቀብሏል።

ስለዚህ ወደዚህ ፍጻሜ ያደርሰን ዘንድ ፍጥረትን ሁሉ ካለመኖር ጨለማ በመስቀል ወደሆነ አስደናቂ ብርኀን ጠርቶታል። የእግዚአብሔር ልጅ መልኩን ካለበሰን ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ “ሰው” መሆን የፍቅሩ ምልዓት መገለጫ የዘላለም ምኞቱ ነው፤ አምላክ በሆነበት ሕላዌ በዚያው መለኮታዊ ማንነቱ ደግሞ ሰው መሆንን ገንዘቡ ሊያደርግ እስኪወድድ ድረስ ገደብ ባለው እና ድንበር በሚገታው እንደ ሰው ባለ ልብ ብቻ ሳይሆን አምላክ በለበሰው የሰው ልብ እስከመጨረሻው ደግሞ አፈቀረን (ዮሐ 13፡1)። ስለዚህ አምላክ በሆነበት መለኮታዊ ፍጽምና እና ምልአት ልክ ፍጹም የ “ሰው” ነት ምልአት ያለው ሰው ሆነ። ሰው በመሆኑ አምላክነቱን አልሰወረም፤ ይልቁንም ሰውነቱ የአምላክነቱ ክብር መገለጥ ምስክር ነው። በዚህም መልኩ እግዚአብሔር “ሰው” በመሆኑ ምሥጢር ውስጥ ዘላለማዊ አምላክነቱ ያለመለያየት፣ ያለመለወጥ እና ያለትድምርት በመገለጡ የጌታ ሰው መሆን ሰው የመሆን ተፈጥሮአዊ ዑደት ምልአት ሳይሆን በእውነትም በአምላክ ልብ ውስጥ ከዘላለም ጀምሮ ተሰውሮ የነበረው የተውነተኛው የሰው ልጅ መልክ መገለጥ ነው። በዚህ ምሥጢር ውስጥ የማይታየው የወልድ መለኮታዊ ማንነት በእግዚአብሔር አብ ልብ ውስጥ በማይደረስበት ምሥጢር እንደተሸሸገ እንዲሁ፤ የእግዚአብሔር አብ የሚታየው የምሕረት መልክ እግዚአብሔር ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ብርኅን ካልሆነ ብስተቀር ሊደረስበት በማይችል ምሥጢር በመካከላችን ተገልጧል[1]። መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን ምሥጢር በሚመለከት ምሥክርነቱን ሲሰጥ “እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል” እያለ ወደ ኢየሱስ ማንነት በትልቀት እንድንመለከት ይጋብዘናል (ዮሐ 1፡26)።

ከዘላለም ጀምሮ በመለኮታዊ ማንነቱ ፍጹም መለኮታዊ በሆነ ባሕርዩ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው እና የሚነግሰው እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በተመላለሰባቸው ዓመታት እንደ ሰው በጊዜ እና በስፍራ ተገለጠ። በዚህ መገለጥ ራሱን ብቻ ሳይሆን አባቱን ጭምር ሊያሳየን ስለወደደ “እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል” (ዮሐ 12፡45) እያለ ዕይታችንን እርሱ ላይ እንድናደርግ ይጋብዘናል። ወደ ቤተልሔም መወረዱም ይሁን እግራችንን ለማጠብ እና በመስቀል እርቃኑን ለመዋል ዝቅ ማለቱ እግዚአብሔር ማን እና ምን መሆኑን ይገልጥልናል። በኢየሱስ ሕይወት የተገለጠው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር የተሰፈረበት መለኮታዊ የፍቅር ዋጋ መጠን ነው።

 

ሴሞ

[1] ቅዱስ ኤሬኒዮስ ዘሊዮን፡- Adv. hear. IV 6፡6.

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት