እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰንበት ዘትንሣኤ

2980 noviy 2000x1200ሰንበት ዘትንሣኤ

መዝሙር፡- ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር.. . .

ንባባት- 1ቆሮ 15፡20-48፣ 1ጴጥ 1፡1-12፣ ሐሥ 2፡ 22-36

ወንጌል፡- ዮሐ 20፡1-18

ስብከት፡ “ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር፥ ንትፈሳሕ ወንትሓሰይ ባቲ፥ ኦ እግዚኦ አድህንሶ፤ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን። አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና”  (መዝ 118፡24-25)

ነገሥታትን አስታረቀ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ሁሉን አዲስ አድርጓል! ምድር በኢየሱስ ደም ታጥባ ፋሲካዋን አድርጋለች፤ ድንበር አስምረው የነበሩት ሔሮደስ እና ጲላጦስ ድንበራቸው ፈርሶ ድልድይ ገንብተዋል። እነርሱ ጠላቶች ሆነው ሳሉ በፖለቲካ ድርድር ሳይሆን በኢየሱስ መካከለኛነት ታርቀዋል። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ትልቁ ቁም ነገር ሁሉተም ነገሥታት ክርስትያኖች አለመሆናቸውን ነው። በእግዚአብሔር ልጅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ በሞቱ ምክኒያት ከታረቁ እና አንዱ የራሱን ነገር ለሌላው ምክር እስኪሰሰጥ ድረስ ከተቀራረቡ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑ እና ክርስትያን ተብለው የሚጠሩ ነገሥታት ወይም መሪዎች በትንሳኤው ለመታረቅ እንዴት ይሳናቸዋል? ሔሮድስ እና ጲላጦስ በኢየሱስ ሞት ከታረቁ የክርስትያን ደሴት ብለን ራሳችንን የምንጠራ በትንሳኤው ካልታረቅን ክርስትናችን እስከ ምን ድረስ ነው? የጌታን ትንሳኤ ስናከብር ትንሳኤ ያላደረኝባቸውን የሕይወት ክፍሎች እንዴት እንመለከታቸዋለን? ጌታ በሀገራችን ነባራዊ እውነታ መካከል ትንሳኤ እንዲያደርግ መፍቀድ እንችል ይሆን? ወይም ደግሞ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ትንሳኤ እንዲያደርግ የማንፈልግበት ክልል፣ ኢየሱስ ትንሳኤ እንዲያደርግ የማንፈልግበት ዘር፣ ኢየሱስ ትንሳኤ እንዲያደርግበት የማንፈቅድበት ሃይማኖት ወ.ዘ.ተ. ሰርተን ከተቀመጥን ቆይተናል። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ እና ሰላም የሚያምን ክርስትያን ቁስለኛ ከማንሳት የዘለለ እና ከዕንባ የከበደ የሰላም ጥሪ ማቅረብ ለምን አቃተው? የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋሲካ መልእክት ከሃይማኖት መሪዎች መልእክት ይልቅ የትንሳኤ ሽታ ያለው ሲሆን ምናልባት ሳናውቀው ቦታ ተቀያይረው ይሆን እንዴ? ያስብላል። የካህናት አለቆች እና የአይሁድ መምህራን በኢየሱስ መቃብር ደጃፍ ወታደሮችን እንዳቆሙት እና ትንሳኤውን ለመጋረድ እንደሞከሩት እንዲሁ ዛሬም ወታደሮች ያቆምንበት የሕይወታችን ክፍል፣ ወታደሮች ያቆምንበት የሀገራችን ክፍል፣ ወታደሮች ያቆምንበት የቤተ ክርስትያናችን ክፍል ወ.ዘ.ተ. የጌታን ትንሳኤ ማደብዘዝ አይቻለውም!

በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከደቦ ፍርድ እና ከፖለቲካ ንግርት በዘለለ ከሔሮደስ እና ከጲላጦስ የከበደ ጠብ የለንም። እነርሱ በኢየሱስ ሞት ከታረቁ እኛ በኢየሱስ ትንሳኤ ልንታረቅ ግድ አለብን። እኛ ወንድማማቾች እንጂ ጠላቶች አይደለንም! ጠላቶች እንደሆንን የተነገረን ትርክት ወንድማማቾች ሆነን ከኖርንበት ዘመን ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ወንድማማችነታችን የጋራ ዕሴቶችን ከመጋራት እና በአንድ መልክዐ ምድራዊ ምሕዋር ወስጥ በመገኘት ወይም የሀገር ልጅ ከመሆን የሚነሳ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ልብ የሚፈልቅ የዘላለም ዕቅድ ፍሬ ነው። በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል እንደመፈጠራችን መጠን የእያንዳንዳችን መልክ ሌላችን ላይ ታትሟል። የተፈጠርንበት መልክ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ እንደ መሆኑ መጠን በመካከላችን መጻተኛ፣ ፀጉረ ልውጥ እና መጤ የለም ይልቁንም በኃጢአት ምክኒያት ለምድር እና ለፍጥረት ሁሉ መጤዎች ሆነን ነበር፤ በኃጢአት ምክኒያት ሁላችንም እርስ በእርሳችን ደግሞ ጸጉረ ልውጦች ነበረን፤ አሁን ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በኩል የአንድ አካል ክፍሎች ሆነናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበኩሉ “ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። ዓይን እጅን። አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን። አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም” (1ቆሮ 12፡21) እያለ ላንለያይ አብረን የተገመድን የክርስቶስ የአካል ክፍሎች መሆናችንን ያሳስበናል።

ይህ ያለንበት ጊዜ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለዓመታት በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች የተቀሰቀሰው ግጭት እና ጦርነት ካደረሰው ውድመት በላቀ መልኩ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ክርስትያን ብሎም እንደ ቤተ ክርስትያን እና እንደ ሀገር የቆምንበትን የጨለማ ጥግ በማይነገር የስቃይ ብርኀን የተጋለጠበት ጊዜ ነው።  የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ስለ አሥርቱ ትዕዛዛት በሚያስተምርበት ክፍል “አትግደል” (ማቴ 5፡21) የሚለውን ሕግ በሚመለከት ሲናገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላቻን እና በቀልን በሚመለከት ራሳችንን እንድንፈትሽ ጥሪውን ያቀርባል። ይህ ጥሪ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሀገራችንን ነባራዊ እውነታ በእውነት ሚዛን እንድንመለከትው የሚያስገድደን ጥሪ ነው! የሰው ልጅ በሕይወት እና በሞት ላይ ጌታ በሆነበት የሀገራችን ሁኔታ ውስጥ ሞት እንደ ቀላል የሚታይ፣ ሞት በየቀኑ የለመድነው፣ ቀስ እያለ የማያስደነግጠን እውነታ ከሆነ ዋል አደር ብሏል። በዚህ የሞት ሽታ ቅርብ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ቆመን ጌታ የሚጠይቀንን ማስተዋል ዳግም ወደ ሕይወት መዓዛ ይመልሰናል።

ጌታ “አትግደል” እያለ ሲያስተምር የማኅበረሰባዊ ሰላም እና አብሮ የመኖር ዕሴቶችን ከማስጠበቅ አንጻር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ነፍስ ማጥፋት በቅድስት ሥላሴ መካከል ያለውን ሰላም እና ስምረት ማወክ ብሎም በአርአያቸው እና በአምሳላቸው የተፈጠረችን ነፍስ ከቅድሥት ሥላሴ እጆች ውስጥ በጉልበት ፈልቅቆ የመንጠቅ ኢፍትሐዊነት በመሆኑ ነው። ይህንን ለማድረግ ከእግዚአብሔር በስተቀር በሞት እና በሕይወት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም የለም! ኢየሱስ በሕማሙ በሞቱ እና በትንሳኤው ሕይወትን ቤዛ አድርጓልና የሕይወት ባለቤት እርሱ ነው! ሕይወት የሚነጠቅባቸው አጋጣሚዎች በምንም መመዘኛ ቢሆን የሞራል ልዕልና እና ይሁንታ የላቸውም፤ በመሆኑም ቤተ ክርስትያን የጌታ ትምህርት ባለ ዐደራ እንደመሆኗ መጠን ይህንን መሰል ሙከራዎችን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ አጥብቃ መቃወምና ከፍትሕ ጎን መቆም ይኖርባታል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ  እየታየ ያለው ግጭት፣ ጦርነት፣ እና ውጥረት ኢትዮጵያ የክርስትና መንፈስ በመካከሏ እየዛለ እንደሆነ ለመመልከት አስችሎናል። ወንጌል በአግባቡ ባልተሰበከበት ሥፍራ ሁሉ ክርስትና ከቀይ መስቀል እና መሰል የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ያነሰ ማኅበረሰባዊ ሚና ይዞ ማነከሱ የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም ሞት እና ትንሳኤ የተጠመቀ ክርስትያን ሁሉ ካህን፣ ነቢይ እና ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እነዚህ መሰረታዊ መልኮቹ መገለጥ ይጠበቅባቸዋል።

በሀገራችን እየሆኑ ያሉት ነገሮች በዛሬው አሁናዊ ሁኔታቸው የሚቀጥሉ ብቻ ሳይሆኑ ይልቁንም እንደ ማኅበረሰብ ለሰው ሕይወት ክቡርነት ያለንን ግንዛቤ ሁሉ ከጥቅም ውጪ የሚያደርጉ እና የሰው ልጅ ሕይወት ክቡርነት “ሰው” ሆኖ ከመፈጠር እውነታ የሚነሳ ሳይሆን ይልቁንም “ሰው” መሆን የሰው ልጅ ካለው የፖሊቲካ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የቋንቋ እና የመልክዐ ምድራዊ ድንበር የሚነሳ እንዲሆን  ያደርጋል። ይህም የሰው ልጅ “ሰው” የሚሆነው ለማኅበረቡ በሚያበረክተው ጥቅም ልክ የሚመዘን እና በማኅበረሰቡ አሁናዊ ሁኔታ የሚወሰን እንጂ “ሰው” መሆን ራሱን ችሎ የሚቆም ገዥ ሐሳብ እንዳይሆን ያደርገዋል።  ይህም ቃል ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን አደረ ከሚለው የክርስትና እምነት መሰረታዊ ቁም ነገር ጋር በእጅጉ የሚጣረስ ነው! የሰው ልጅ በሥጋ እና በነፍስ የቆመ ምክኒያታዊ ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን እኛን አይመስልም የምንለው ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ከመፈጠሩ የተነሳ ቁርጥ እኛን ይመስላል። ድንበር ለምድራዊ ነገር ወሰን ሆኖ እኛን ከሌላው የለየን ሊመስለን ይችላል፤ ምናልባትም “እነሱ” እና “እኛ” በሚል ግንዛቤ ቅጥር ሰርተን የራሳችን እስረኞች ሆነን ይሆናል፤ ነገር ግን ከዘላለማዊ ፍጻሜያችን አንጻር ሲታይ ይህ ጥቅሙ እጅግም ነው!   

በሰማያዊው ሀገር እኛን የሚመስል ሰው ሳይሆን እግዚአብሔርን ይመስሉ ዘንድ በልጁ መልክ መለኮታዊ ውበት ያገኙ ከልጁ መልክ የተነሳ ጉራማይሌነት ጠፍቶ በአንዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ የተገለጡ ወንድሞች እና እኅቶች ናቸው። በቅድስት ሥላሴ ስም የተጠመቀ ክርስትያን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነት የሚያደንቅ እና የሚያከብር፣ በልዩነት ውስጥ ያለውን መለኮታዊ አንድነት የሚያሰላስል ፍጥረት እንጂ በልዩነት ጽንፍ የሚይዝ ፍጥረት ሊሆን አይችልም። እርሱ ከእኔ ጋር ለመኖር ሥፍራ የለውም የሚለው ሐሳብ ከቅድስት ሥላሴ ጋር የሚጣረስ ከክርስትና ጋር ሆድ እና ጀርባ የሆነ ሾተላይ ሐሳብ ነው።  በመሆኑም ክርስትያን ሆኖ የተጠመቀ ሁሉ ከሌሎች ጋር በአንድ ድምጽ በመንፈስ ቅዱስ ልሳን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር የሚዘምር የአምልኮ ኅብረት እንጂ በልዩነት ቀንበር ሥር የሚበዘበዝ ባርያ አይደለም። በወገንተኝነት ባርነት እና ጨለማ ውስጥ የሚሰቃይ “አማኝ” ሁሉ የክርስቶስን የማዳን ኃይል የጣለ ከመሆኑ የተነሳ እምነቱ ክርስትና ተብሎ ሊጠራ የማይቻል እና በመዳን መንገድ ላይ ወንዝ የማያሻግር ርዕዮተ ዓለም ነው! ከዚህ ባርነት ወጥተን የጌታን ትንሳኤ ለማክበር ሁለንተናዊ ዕርቅ ማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው!

የጌታ ትንሳኤ በመካከላችን ሥፍራ እንዲኖረው እኛ ራሳችን ከራሳችን ጋር፣ ከፍጥረት ሁሉ ጋር፣ ከሁሉም በላይ በቅድስት ሥላሴ መልክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በኩል ወንድም እና እኅት ከሆኑን የሰው ልጆች ሁሉ ጋር የታረቅን መሆን ይገባናል። እርሱ ስለ ኃጢአታችን ከሞተ እና ፈራጅ ሆኖ ሳለ ስለ እኛ በሰው ይፈረድበት ዘንድ በትህትና እጆቹን ወደኋላ ታስሮ በፍርድ ወንበር ፊት ከቆመ እኛ በእርሱ በኩል ባገኘነው የጽድቅ ጸጋ የሌሎችን ኃጢአት ይቅር የማንልበት እና ፍርድን ትተን ምኅረትን የማንለማመድበት ትንሳኤ ሊኖር አይችልም።

የማርቆስ ወንጌል 16፡8 ላይ የጌታ መልአክ ለሴቶቹ የትንሳኤውን የምሥራች እንዲያበስሩ የስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ሲሰጣቸው እንመለከታለን፤ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ እኛም ዕጣ ክፍል አለን! እኛም ለጌታ ወንድሞች የትንሳኤውን የምሥራች ለመናገር ተልከናል፤ ነገር ግን ለጌታ ወንድሞች የሚለው ሐሳብ ከጌታ ወንድምነት የምንቀንሳቸው ሰዎች፣ ቋንቋዎች፣ ድንበሮች እና “እነሱ” እያለን የምናርቃቸው ወገኖች የሉም። የጌታ ወንድምነት ከእርሱ ዘላለማዊ ልጅነት የተገኘ የጸጋ ሥጦታ እንጂ እኛ የደቦ ፍርድ ሰጥተን የምናሳልፍበት ወይም በድምጽ ብልጫ የጌታ ወንደሞች ሊሆኑ የሚገባቸውን የምንመርጥበት ሥልጣን የለንም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትንሳኤ የተሰጠንን አዲስ ማንነት እያስታወሰን “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል። በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ” (ቆላ 3፡10-12) ይለናል።

በዛሬው የመጀመርያ ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል” (1ቆሮ 15፡43) እያለ ዛሬም ለሥራ እንድንነሳ ይጋብዘናል። ዛሬም ሁሉ ያለቀለት በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ ለሰላም ድምጻችንን ከፍ እንድናደርግ፣ ከአመጽ ጩኸት በላይ የሰላም ጽሞና ወደ እያንዳንዱ ልብ ሰርጾ እንዲሰፍን ልንንቀሳቀስ ይገባናል። በእርግጥ ስለ ሰላም መናገር በደቦ ፍርድ ውርደት ያስከትልብን ይሆናል፣ በርግጥ አብረን መፍረድ እንጂ አብረን መውደድ አልተፈቀደልን ይሆናል፤ ነገር ግን በውርደት የምንዘራውን በክብር የሚያነሳው አሸናፊው ኢየሱስ ድል ነስቶ የዚህን ዓለም አመጽ እና ጩኸት ሁሉ ባዶ አስቀርቶታል! ስለዚህ ከሁከት ዋይታ በላይ የሰላም ቅንጣት የበለጠ ኃይል አለው! ከጴጥሮስ ሰይፍ ይልቅ የጌታ መስቀል የበለጠ ፈዋሽ ነው! ነገር ግን አሁን ያለንበት ወቅት የፈተና ወቅት ነው፤ ጊዜው በአምባገነን ጩኸት ፊት የጌታን ጽሞና እና በጲላጦስ ፊት የነበረውን አርምሞ የምንለማመድበት ወቅት ነው። በሰላም ዝምታ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ይናገራል!

ሁለተኛው ንባብ ያለንበትን ሁኔታ እያስታወሰ ያጽናናናል፤ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል” (1ጴጥ 1፡6-7) እያለ ሁኔታችንን ጠቅለል አድርጎ ያስቃኘናል። በፈተና ማዕበል መካከል ብንሆኑም ፈተናን ታግሶ ያሸነፈ እና የሞትን መውጊያ የሰበረ የክብር ጌታ ልጆች መሆናችንን እንዳንረሳ ይመክራል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በኩል  ከአሸናፊዎች ሁሉ እንደምንበልጥ እያስታወሰን በጌታ ያለንን እምነት የተፈተነ ወርቅ እያለ ይገልጸዋል። ቆሻሻው እና ዝገቱ ጊዜ ይፈልጋል እንጂ ሥፍራውን መልቀቁ አይቀርምና ቆሽሿል ተብሎ ወርቁ አይጣልም፤ ነገር ግን ዝገቱን ስናስለቅቅ ወርቁ ራሱ ደግሞ እንዳይጠፋብን መጠንቀቅ ይገባናል! የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና” (ሐሥ 2፡25) እያለ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስንመላለስ ብቻችንን እንዳልሆንን፣ የትንሳኤው ጌታ ከእኛ ጋር መሆኑን እንድናስተውል ይጋብዘናል። ትንሳኤ ጌታን ፊት ለፊት እያዩ መኖር ነው። ትንሳኤ በወንድሞቼ እና በእኅቶቼ ውስጥ የትንሳኤውን ጌታ መመልከት እና ለእርሱ በሚገባ ክብር ከእነርሱ ጋር በሁለንተናዊ የሕይወት ዑደት ውስጥ በሰላም መኖር ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ የጌታን ትንሳኤ ሲተርክልን ሐዋርያቱ ከጌታ ስቅለት በኋላ በከፍተኛ ፍርሃት እና የወደፊቱ ሁኔታ በሚያመጣው ነገር በመጠራጠር በር ዘግተው ተቀምጠው እንደነበር ይናገራል። ተስፋ ያደረጉት ሁሉ የሚሆን ያለመሰላቸው ሰሞን በሁሉ ነገራቸው ላይ በር ዘግተው ነበር፤ ነገር ግን ፍርሃቱ እና ጥርጣሬው በልባቸው ነግሶ ስለነበር በር ዘግቶ መቀመጥ ነጻነት የሚሰጣቸው መተማመኛም አልነበረም። ከውጪ ከሚመጣባቸው አስደንጋጭ ነገር ይልቅ በልባቸው የሚያስደነግጣቸው ነገር የበለጠ የከፋ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሳለ፣ በሕይወት እና በሞት ጥያቄ መካከል፣ በተስፋ እና በጥርጣሬ ትግል ውስጥ በማዕበል ሲናጡ፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ሁሉ ያለቀለት ሲመስላቸው፤ ያን ጊዜ፣ አዎ ያን ጊዜ ጨለማን ሁሉ የሚገልጥ፣ ወደ እውነት እና ወደ ጽድቅ የሚመራ ጌታ ወደ እነርሱ መጣ!  “አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው” (ዮሐ 20፡19)። ኢየሱስ በሀገራችን፣ በቤተሰባችን፣ በቤተ ክርስትያናችን እና በእያንዳንዳችን ሕይወት መካከል ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን በሚል ሰላምን እና ዕረፍትን በሚሰጥ ሰላምታ ያነጋግረን!

የተቀደሰ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ይሁንልን!

ከመ በኩሉ ይሴባህ እግዚአብሔር!

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት