ልደተ-ማርያም
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Sunday, 08 May 2022 23:20
- Written by Super User
- Hits: 1119
- 08 May
ልደተ-ማርያም
የግንቦት ወር ከጥንት የክርስትና ዘመን አንስቶ ለእመቤታችን ማርያም ክብር የተሰጠ ወር ነው። በምዕራቡም ይሁን በምሥራቁ ዓለም ይህ የግንቦት ወር እመቤታችንን ማዕከል ያደረገ መንፈሳዊነት የሚዘወተርበት፣ በርካታ ንግደቶች ወደ ታላላቅ የእመቤታችን የጸሎት ሥፍራዎች እና ገዳማት የሚደረጉበት ወር ነው። ር.ሊ.ጳ. ፍራቺስኮስ እ.ኤ.አ. በግንቦት 1 ቀን 2022 ዓ.ም. በወርኃ ትንሳኤ ዑደት ውስጥ በሚያደርሱት “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” (Regina Coeli) በተሰኘው ጸሎታቸው ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝበ እግዚአብሔር ባስተላለፉት መልእክታቸው፣ “ወርሃ-ግንቦት፣ ወርሃ-ማርያም” በመሆኑ ምዕመናን በዚህ ወር ከእመቤታችን ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ጉዞ የበለጠ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በሀገራችን የሰላም ዕጦት በሰፈነበት በዚህ ወቅት የሰላም ንግሥት የሆነችውን እመቤት አማላጅነት እንድንጠይቅ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታው ያስገድደናል። የእመቤታችንን ልደት ስናከብር ከእርሷ ጋር አብረን የፍጥረትን ልደት ሁሉ እናከብራለን። ፍጥረት ሁሉ በተፈጠረበት ክብር መታየት የሚችለው በሰላም እና በወንድማማችነት መንፈስ እርስ በእርስ መቀባበል ስንችል ነው። ጌታ በመስቀሉ የጥልን ግድግዳ እንዳፈረሰ የምናምን የጥል ግድግዳ ለመገንባት በነፍስ ዋጋ የጥላቻ ጡብ ጠርበን ማዘጋጀት አንችልም።
የእመቤታችንን ልደት ስናከብር ፍጥረትን ሁሉ በማንነቱ ምልዓት መቀበል መቻልን ይጠይቃል፤ የፍጥረትን ማንነት እንደተፈጠረበት መለኮታዊ ዓላማ ክብር፣ ከሁሉ በላይ የሰውን ልጅ ሰው ሆኖ በተፈጠረበት የአምላክ አርአያ እና አምሳል ክብር መቀበል፣ ብሎም ዋጋውን ከተፈጠረበት መለኮታዊ መልክ እና ከተገዛበት የደም ዋጋ አንጻር መገንዘብ ካልቻልን የእመቤታችንን ልደት ማክበሩ ስለ ልደት ያለንን ግንዛቤ ትዝብት ውስጥ ይከትተዋል።
በዓላቶቻችን ለእግዚአብሔር ክብር በቅዱሳኑ አብነት የምሥጋና ፍሬ የሚቀርብባቸው ከመሆን ይልቅ የውድድር እና የብሽሽቅ መድረክ ከሆኑ ዋል አደር ብለዋል። ሌላውን በማዋረድ የበለጠ የምናከብረው የሚመስለን እግዚአብሔር የራሳችን ጠብ እና ጉልበተኛነት ነጸብራቅ ነው፣ በፍቅር እና እንደ ጌታ ባለ የታዛዥነት ብዕር ከመስቀሉ በሚፈሰው የደም ቀለም ሳይሆን ይልቁንም በጦር በሚፈስ እና በጉልበት በሚመካ “ወንጌል” የምናከብረው ወይም “የምናስከብረው” እግዚአብሔር የለም።
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአርአያው እና በአምሳሉ ፈጥሮታል ብሎ የሚያምን አማኝ ሁሉ በሌላው ላይ የሚወረውረው ድንጋይ፣ የሚሰነዝረው ስድብ፣ ስም ማጥፋት፣ አክራሪ ብሔርተኝነት እና አክራሪ ሃይማኖተኝነት ወ.ዘ.ተ. አመልከዋለሁ በሚለው በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዘር አይደለምን? ጌታ በገዳዮቹ በተያዘ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ አብዛኞቻችን አይነት አቋም ነበረው፤ በጉልበት ሁሉን መስመር ማስያዝ፣ በጦር ሰላም ለማምጣት ስለቱን ከሰገባው ስቦ መንቀሳቀስ፤ ነገር ግን ጌታ እንዲህ ያለውን መንገድ አጥብቆ ይጸየፈዋልና “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?” (ማቴ 26፡52-53) እያለ ስለምናደርገው ነገር ኢ-ፍትሐዊነት እና ኢ-ምክኒያታዊነት ይናገራል።
ነገር ግን ይህ የጌታ መስቀል ሌላ ጠለቅ ያለ ነገር እንድንመለከት በሩን ይከፍትልናል። ይህም እመቤታችን በጌታ መስቀል ሥር የነበረችበት ሁኔታ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ የጌታን ስቅለት በሚመለከት ሲናገር “በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ ማርያም ቆማ ነበር” (ዮሐ 19፡25) ይላል። ይህ የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ምልከታ እመቤታችንን እጅግ በተለየ ዕይታ እንድናስተውላት በር የሚከፍትልን ቁም ነገር ነው። ስለ እመቤታችን ያለን ምልከታ እና ግንዛቤ አብዛኛውን ጊዜ ከኀዘኗ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ከእመቤታችን ጋር የተገናኙ መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ከኀዘንተኛይቱ እመቤታችን ጋር የተሳሰሩ ናቸው፤ ለምሳሌ ያህል በቤተ ክርስትያናችን የሚዘመሩ መዝሙሮችን ብንመለከት በዚሁ ዐውድ የተቃኙ ሆነው እናገኛቸዋለን። “የፍቅር ዕንባ” የተሰኘው የእመቤታችንን ኀዘን የሚያዜም መዝሙር የሚከተለውን ሐሳብ በጉልህ ያሰማል፡-
“ልጇ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያየች የፍቅር ዕንባዋን እጅግ አፈሰሰች
አዛኚቱ እናቱን ለእኛም ሰጥቶናል የፍቅር ዕንባዋ ስለኛም ይፈሳል
የፍቅር ዕንባ ×2
እናት አለችን ሁሌ የምታነባ”
ነገር ግን አጠገቧ ሆኖ የዚህችን እናት ጽናት የተመለከተው ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ዕንባዋ ሳይሆን በመስቀሉ እግር ሥር በጽናት ስለመቆሟ ይመሰክራል። እመቤታችን በልጇ መስቀል ሥር የቆመችው በእግሯ ብቻ ሳይሆን በነፍሷም ጭምር ነበር፤ ስለዚህ በታላቅ ጽናት፣ በታላቅ እምነት በዚያ ቆማ ልጇን ትመለከተው ነበር። ዕይታዋን ከልጇ ላይ ለአፍታ እንኳን ስላልመለሰች የቤተ ክርስትያን ምሳሌ ሆና ትታያለች። በመስቀሉ ሥር ሳለች ጸሐይ እና ጨረቃ ሲጨልሙ፣ ምድር ስትናወጥ፣ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ሲከፈል፣ እመቤታችን በመስቀሉ ሥር እንደቆመች፣ ዐይኖቿን በልጇ ላይ እንደተከለች ነበረች። የልጇ እንዲህ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ መዋል፣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር የሚነዝር ኀዘን በነፍሷ መካከል እያለፈ እርሷ ግን ለአፍታም ቢሆን ዕይታዋን ከልጇ ላይ አላነሳችም ነበር። ይልቁንም ሁሉንም ትመለከታለች፣ ታስተውላለች፣ ምሥጢሩን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስለዋለች፤ በዚህ መስቀል ሥር ቢሆን እንኳን የእርሷ መልስ “እነሆኝ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ” የሚል ነው።
እመቤታችን በጎልጎታ በልጇ መስቀል ሥር ስትቆም ከማልቀስ የገዘፈ፣ ደረት ከመምታት አሻግሮ የሚመለከት የመዳን ምሥጢር ፍጻሜ ምሥክርነት ሥራ ነበረባት። እርሷ እያንዳንዳችንን ወክላ በዚያ ነበረች፤ ለእምነት አባታችን ለአብርሐም እና እንደ ልቤ የሆነልኝ ተብሎ ለተጠራው ለንጉሥ ዳዊት የተሰጣቸው ተስፋ፣ የሰሎሞን እና የዳንኤል ጥበብ፣ የነብዩ ኤልያስ እና የመጥምቁ ዮሐንስ ከእሳት የሚፋጅ ጌታን በክብሩ የማየት ናፍቆት ሁሉ በእመቤታችን ልብ ውስጥ ትርጉም አግኝቶ በዚያ መስቀል ሥር ጥልቅ በሆነ አርምሞ የአምላክን ምሥጢር ስታሰላስል እንመለከታታለን። በዚያ መስቀል ሥር ለዘመናት ተዘግተው እና ዝገው የነበሩት የጥበብ በሮች ተከፍተው ይጣራሉ (ምሳ 1፡20-21)፤ እመቤታችን በእነዚያ ሦስት ሰዓታት በዚያ ቆማ የነብያትን ተስፋ ፍጻሜ እና የአዲስ ኪዳን ተስፋ ሥጦታን ትመለከታለች። እርሷ በነፍሷ ከልጇ ጋር አብራ በመስቀል ላይ ስለነበረች በርግጥም ከልጇ መስቀል ጋር በእውነት በጎልጎታ ተተክላለች።
የሉቃስ ወንጌል ስለ ታታሪ አገልጋይ “ደስታ እና ምሥጋና” ሲናገር “ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው... ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 12፡37-38) ይላል። ጌታ ብቻውን በተተወበት፣ የወዳጆቹ ክህደት ከሌሊት ጨለማ በገዘፈበት፣ ፍጥረት በሙሉ በኃጢአት ከባድ እንቅልፍ ተይዞ በደከመበት፣ ጸሐይ እና ጨረቃ ተማክረው በጨለሙበት የጎልጎታ ሌሊት እመቤታችን በመስቀሉ ሥር ነበረች። በዚያ ጸሐይ ብርኀኗን በከለለችበት የጎልጎታ ሌሊት በመስቀሉ ሥር አንድ የምታበራ የእምነት ጧፍ እመቤታችን ብቻ ነበረች።
ይህቺ ሴት አምላክን በማኅጸና ከመለኮታዊ ክብሩ ጋር ስትሸከም ጽናትን ተምራለች፤ በመስቀሉ ሥር ያንን ልጇን በልቧ ባለው እምነት ከመለኮታዊ ክብሩ ሁሉ ጋር እየተመለከተች፣ እነዚያን ዘጠኝ ወራት እያሰበች ትበረታለች፤ ምክኒያቱም ከእነዚያ ዘጠኝ የምጥ ወራት በላይ አሁን በመስቀል ላይ ፍጥረት በሙሉ እንደ አዲስ እንደሚወለድ አምናለችና ነው። እርሷ ከመስቀሉ የሚፈልቀውን ደም እና ውኃ በክብር ጠብቆ እንደሚይዝ ንጹሕ የአምልኮ ጽዋ በዚያ ሆና ራሷን ለጸጋ ሥጦታ ሁሉ ክፍት አድርጋ ትታያች። በፍጥረት እና በፈጣሪ መካከል በዚያን ቀን በመስቀሉ ሥር የነበረችው የሰንሰለቱ የመጨረሻው ዘለበት እመቤታችን ራሷ ነበረች፤ ይህ ዘለበት ልጇን ቀና ብላ የምታይበት እና ሁሉን ነገር በልቧ ጠብቃ የምታሰላስልበት፣ ገና በወጣትነቷ የጉብዝና ዘመን “እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ” ያለችበት እምነት ነው። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በተራራው ላይ ቆይቶ በተመለሰ ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር በፊቱ ላይ ስለነበር ፊቱ ያበራ ከነበረ (ዘጸ 34፡29-34)፤ የእመቤታችን ክብር እንዴት ያንጸባርቅ ይሆን? ክብሯስ በቅዱሳን መካከል እንዴት ባለ ብርኀን የሚገለጥ ይሆን?!
አንዳንድ ጊዜ በስቃይ መካከል ያለን ፍሰሐ ለማየት ከባሕርያዊ ዐይኖቻችን ባሻገር በመንፈስ ቅዱስ የተኳለ ዐይን ያስፈልገናል (ኤፌ 1፡18-19፣ ራዕ 3፡18)፤ በተናደደ ሰው ፊት ላይ የቁጣን እሳት እንደምንመለከተው ሁሉ በቅዱሳኑ ፊት ላይ በጌታ ያመኑበት ጽናት እና በመከራ መካከል እስከመጠጨረሻው ጸንተው የቆሙበትን እምነት ማንበብ እና መማር እንችላለን። ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ከእመቤታችን ደግሞ እምነት ሥጋ ለብሶ እንዴት እንደተኖረ እና እንዴት እንደታመነ እንማር ዘንድ በመስቀሉ ሥር ቆማለች። ይህ የእምነት ትምህርት በፊደል ሳይሆን ይልቁንም በነፍስ ከጌታ ጋር በመስቀል ላይ በመዋል የምንማረው ቁም ነገር ነው። እግዚአብሔር ዓለምን እንደ አዲስ በፈጠረበት ጊዜ በቤተ-ልሔም በምጥ ላይ ከነበረችበት ይልቅ በአዲስ ልደት ምጥ ተይዛ በመስቀል ሥር የነበረችው እመቤት እግዚአብሔርን ማመን ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መታመን ምን እንደሆነ በተግባር በተኖረ እምነት ልታስተምረን በመስቀሉ ሥር ቆማለች።
መልካም የልደተ-ማርያም በዓል ይሁንልን!
ሴሞ