ፍቅር (ክፍል ፪)
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Saturday, 19 November 2022 19:21
- Written by Super User
- Hits: 946
- 19 Nov
ፍቅር (ክፍል ፪)
ቅዱስ ቶማስ አኳይናስ የፍቅርን መሰረታዊ ይዘት እና ምንነት ለመተርጎም በሚያደርገው ጥረት በክፍል ፩ የተመለከትናቸውን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ለማጥራት ይሞክራል። አኳይናስ ፍቅርን በጓደኝነት ጥላ ስር አስቀምጦ የፍቅርን ትርጉም እና ልክ እንደ አዲስ እንድንመለከተው ይጋብዘናል። ፍቅር በጓደኝነት ዐውድ ውስጥ የሚገለጠው በጓደኝነት ውስጥ አንዱ ለሌላው የሚሰጠው ለማንነቱ ተገቢ የሆነ ስፍራ በግልጽ ስለሚታይ ነው። ብሉይ ኪዳን ይህንን የጓደኝነት ልክ ሲያመላክተን በዳዊት እና በዮናታን መካከል የነበረውን ወዳጅነት እያሳየን “ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ” (1ኛ ሳሙ 18፡3) ይላል። ቅዱስ ቶማስ አኳይናስ በታላቁ የነገረ መለኮት መዝገብ Summa Theologie (Question 23, article 1) በጥያቄ 23 አንቀጽ 1 ስር በሚያደርገው ማብራርያ ፍቅር ከሌሎች ጋር የምንካፈለው የጋራ የሕይወት ቁም ነገር እንጂ የግል መገለጥ እንዳልሆነ እንድንረዳ ይጋብዘናል። እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ስለገለጠ እና ስላነጋገረን፣ ከእኛ ጋር ወዳጅነት ስለመሰረተ እና በመንፈስ ቅዱስ ስራ በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደዚህ ወዳጅነት እንድንገባ ስላደረገን ፍቅር ሁልጊዜ የኅብረት ምስጢር ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ ይህንኑ ቁም ነገር እንዲህ እያለ ይናገራል፡-
“ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል” (1ኛ ዮሐ 4፡9-11)።
የእግዚአብሔር መገለጥ እና በታሪካችን ውስጥ መገኘት የፍቅር ታሪክ ሁሉ ማሰርያ ውል ነው። ከእግዚአብሔር መገለጥ የተነሳ እኛ ደግሞ በተፈቀርንበት ፍቅር ማፍቀር እንችል ዘንድ በጦር ተወግቶ ወደ አብ የምናይበትን የመገለጥ መስኮት እንደከፈተልን፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አይነት፣ ማፍቀር ስራው የሆነ አዲስ ልብ በምሥጢረ ጥምቀት ተቀብለናል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” (2ኛ ቆሮ 2፡16) እያለ ያስታውሰናል፤ ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ በእያንዳንዳችን ውስጥ አባቱን የሚያፈቅርበት፣ የሚወድስበት እና ስለ ስሙ ክብር ሁሉን በተዓዝዞ የሚቀበልበት ትህትና ነው። በመሆኑም ፍቅር የእኔ እና የወዳጄ የጋራ ስምምነት ሳይሆን እውነተኛ ፍቅር ኢየሱስ በልቤ እና በነፍሴ ውስጥ መስቀሉን የሚተክልበት ፈዋሽ ስቃይ ነው።
ኢየሱስ በእኔ ልብ ሊያፈቅር በልቤ ነጻነት መጠን ራሱን ይገልጣል፤ በዚህም ምክኒያት በወንድ እና በሴት መካከል ያለው ፍቅር ኢየሱስ ራሱን ለቤተ ክርስትያን በሰጠበት ፍቅር መገለጡ፣ ፍቅር በማፍቀሩ እንድናፈቅር የሚያስችለን ጥበብ መሆኑ ማሳያ ነው። ኢየሱስ ቤተ ክርስትያንን በማፍቀሩ እና ራሱን ለእርሷ አሳልፎ በመስጠቱ እርሷ ደግሞ እንደ አዳኟ ተቀብላ እንድታፈቅረው ከፍቅሩ ጉልበት የተነሳ ልቧን የምትከፍትበት መተማመን አላት። ስለዚህም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ወዳጅነታቸው ሲናገር “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ” (ዮሐ 15፡15) እያለ ወደዚህ መገለጥ ሲጠራቸው እንመለከታለን። ፍቅር በበጎ ኅሊና በሚደረግ የልብ ልውውጥ የሚገለጥ ጓደኝነት ነው፤ በዚህ ልውውጥ ውስጥ የሌላውን ነጻነት የሚያከብር እና ከሌላው የማይጠብቅ መለኮታዊ ጨዋነት በመኖሩ ቅዱስ ጳውሎስ የፍቅርን ባሕርያት ሲዘረዝር ይህንን በመለኮታው ጨዋነት የተገራ ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ብስለት ታሳቢ በማድረግ እንዲህ ይላል፡-
“ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል” (1ኛ ቆሮ 13፡ 4-7)።
ይህ መለኮታዊ ፍቅር በጓደኝነት ምሥጢር ውስጥ የበለጠ ይገለጣል ካልን በዚህ ረገድ የሚነሳው ሌላው ቁም ነገር የወዳጅነት እኩሌታ ጉዳይ ነው፤ ይህም ማለት ለጓደኝነት ሁለት አንድ አይነት ተፈጥሮ ያላቸው፣ ዓላማቸውን አንድ ያደረጉ እና ወደዚያውም ለመድረስ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉ ፍጥረታት ያስፈልጉናል። ይህም ማለት በምክኒያታዊ መንፈሳዊት ነፍስ እና በሥጋ የቆሙ ሁለት ሰዎች ያስፈጉናል ማለት ነው። እነዚህም አንዱ ለሌላው ባለው መልካም ነገር ወደ ፍጻሜ ይደርሱ ዘንድ ድካምን ሳይቆጥሩ በበጎ ኅሊና ይህንኑ መልካምነት ለማሳካት ራሳቸው አሳልፈው የሚሰሰጡ ወዳጆች ናቸው። ኢየሱስም ስለዚህ ጓደኝነት ሲናገር “ነፍሱን ስለወዳጆቹ አሳልፎ ከመስጠት የበለጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ 15፡13) እያለ ይናገራል። በመሆኑም ይህንን ምሥጢር ያስተምረን ዘንድ እግዚአብሔር ራሱ ሰው ሆነ፤ “በመካከላችን አደረ” (ዮሐ 1፡14)። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ደግሞ ወዳጅነት ይኖረን ዘንድ፣ በፍቅሩ ጉልበት እናፈቅርበት ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በአዲስ ልደት መታጠብ ከባርነት ጌታን ሳያዩ የመኖር ጨለማ አውጥቶ፣ ከጌታ ጋር በማዕድ ወደመቀመጥ የጓደኝነት ክብር ከፍ አደረገን።
እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእርሱ የነበረውን ጸጋ በእኛ ላይ ስላፈሰሰው እና በጸጋው ነጻነት ወደ መለኮታዊ ፍቅር ከፍ ስላደረገን የፍቅር መሰረቱ ሥጋ ለብሶ የተገለጠው ወደዚህ ክብር ከፍ ያልንበት የእግዚአብሔር መልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው የመጀመርያይቱ መልዕክቱ ስለዚህ ቁም ነገር ሲመሰክር፡- “ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው” (1ኛ ቆሮ 1፡9) እያለ ወደ መለኮታዊ ኅብረት እንደተጠራን እና የዚህን ኅብረት መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሆነ ያሳየናል። ክርስቶስ የዚህ ኅብረት መሰረት ከሆነ፣ በዚህ ኅብረት ውስጥ ስፍራ የሌለው ፍጥረት ባለመኖሩ “ጠላቶቻችሁን ወደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ መርቁ እንጂ አትርገሟቸው” (ማቴ 5፡44-45፣ ሉቃ 6፡28፣ ሮሜ 12፡14) የሚለው የጌታ ትዕዛዝ በዚህ መነጽር ሲታይ የበለጠ ትርጉም ይሰጠናል።
ይህንን የጌታን ጥሪ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ክትተን ብንመለከተው የበለጠ በቀላሉ ለመረዳት ያስችለናል። የልብ ጓደኛ ሲኖረን እርሱን ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ኅብረት ያላቸውን ሁሉ በተቻለን መጠን ለማወቅ፣ ለማክበር እና ለማፍቀር ዝግጁ ነን። ቤተሰቦቹን፣ ጓደኞቹን፣ የሥራ ባልደረቦቹን፣ በሕይወቱ ዋጋ የሚሰጣቸውን ነገሮች፣ ቦታዎች፣ በዓላት እና የመዝናኛ ምርጫዎችን ሳይቀር በልዩ ጥንቃቄ ለመያዝ የተቻለንን እናደርጋለን። በመሆኑም ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከልጁም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት እንደሚያደርግ ሰው እግዚብሔር የሚወዳቸውን ደግሞ ልንወድ ይገባናል። ጠላቶቻችሁን ወደዱ የሚለው የጌታ ቃል የጠላቶቻችንን አሁናዊ ማንነት የሚመለከት ጥሪ ሳይሆን ይልቁንም እግዚአብሔር እነርሱን ከወደደበት ከዚያ ፍቅር ጋር ኅብረት ስላለን እና በዚያ ፍቅር በተከፈለ ዋጋ በአንድ ቤዛነት ስለተዋጀን ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ እንዲህ ይላል፡-
“በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ...ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና” (1ኛ ዮሐ 2፡9-11)።
ነገር ግን ዮሐንስ የዚህን በጨለማ የመመላለስ እውርነት “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ” (1ኛ ዮሐ 3፡15) በማለት የዚህን ጨለማ ጥልቀት ያሳየናል። ነፍሰ ገዳይነት የሰውን ልጅ በቀጥታ መግደል ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሲሞት ቆሞ ማየትም ጭምር ነው። የሰው ልጅ በወንጌል ብርኀን እጦት ከእግዚአብሔር ልጅነት ክብር ወርዶ በዲያብሎስ የባርነት ቀንበር ሲበዘበዘ ቆሞ ማየት ከነፍሰ ገዳይነት ተለይቶ አይታይም! በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ቤዛነት የተገዛች ነፍስ ስትጠፋ ቆሞ ማየት የተገዛችበትን ዋጋ እና ክብር በተዛባ ሚዛን መመዘን እና ለክርስቶስ ደም ያልተገባ ዋጋ መተመን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ቤዛነት እንደመገዛታችን መጠን እርሱ መለኮታዊ ክብሩን የተወለትን፣ ስለ እርሱ መዳን የባርያን መልክ የለበሰለትን እና በደሙ ክብር አርነት ያወጣውን ሰው እኛ በራሳችን ክብር ግብዝነት ከመዳን ኅብረት ልናስወጣው አንችልም! ይልቁንም በብርኀን እንደሚመላለሱ ልጆች ጠላቶቻችንን መውደድ በብርኀን የመመላለሳችን መገለጥ ምሥክር ነው። የክርስቶስ ኢየሱስ መሆናችንን የምንመሰከረው በጋራ ባለን እምነት፣ በጋራ ባለን ሥርዐተ አምልኳዊ ትስስር ወይም በጋራ ባለን የስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ሳይሆን ከእነዚህ ሁሉ በፊት በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ከተፈጠርንበት ቁም ነገር የተነሳ እግዚአብሔር እንደተቀበለን እኛ ደግሞ ራሳችን መቀባበል እና መዋደድ ስንችል ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ቆመን የምናደርገው የስብከተ ወንጌል ሥራ ሁሉ ከሌሎች የርዕዮተ ዓለም ፕሮፖጋንዳዎች የተለየ ገጽታ አይኖረውም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ!” እያለ ይህ የደስታ ኅብረት በቅድስት ስላሴ መካከል ያለ የፍቅር ልውውጥ በሰው ልጆች መካከል ደግሞ ይገለጥ ዘንድ ጥሪውን ያቀርባል። ይህ በቅድስት ሥላሴ መካከል ያለው ፍቅር በእኛም ሕይወት ይገለጥ ዘንድ ጌታ ለባሕርያችን በተገባ የደስታ ሥጦታ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከባሕርያችን ውሱንነት ባሻገር መልዕልተ ባሕርያዊ በሆነ በቅድስት ሥላሴ መካከል ባለ ሐሴት ነፍሳችንን ያረካት ዘንድ በመስቀል ላይ ሆኖ “ተጠማሁ!” (ዮሐ 19፡28) እያለ ይጣራል። ኢየሱስ የሚጠማው ቁም ነገር እያንዳንዳችን ደግሞ ከእርሱ ጋር እውነተኛ ጓደኝነት እንዲኖረን እና በእርሱም ላይ እንደ አንድ አካል ሆነን እንደመጋጠማችን ቁም ነገር እርስ በእርሳችን ደግሞ እርሱ እኛን ባፈቀረበት ፍቅር እንፋቀር ዘንድ ነው።
በዚህ አይነት በቅድስት ስላሴ መካከል ያለው κοινωνία የፍቅር ኅብረት በእያንዳንዳችን ሕይወት ከራሳችን፣ ከማንነታችን፣ ከታሪካችን እና ከፍጥረታችን ጋር፣ ብሎም ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ይገለጥ ዘንድ እያንዳንዳችን በአንዱ እውነተኛ የአብ መልክ ተስለን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት የአግዚአብሔር አብ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ሆነን አባ አባት እያልን በመንፈስ ቅዱስ ልሳን እርሱን በአንድ ምሥጋና እንወድሰው ዘንድ ለክብር መዝሙር ተመርጠናል። በቅድስት ሥላሴ ኅብረት መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች ሆነን ስለተሳተፍን የዚህን ኅብረት ሰዋሰው እና ባሕርይ እየተለማመድን እናድጋለን፤ በዚህም አይነት የዚህ ኅብረት ሰዋሰው የሕይወት ታሪካችን እንደ አዲስ የተጻፈበት ቋንቋ በመሆኑ ይህንን ሰዋሰው እያጠናን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙላት እስከምንደርስ ድረስ ወደፊት እንዘረጋለን። ይህ ሕይወት በጸጋ ከፍ ወዳለው ስፍራ የሚነጠቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ እንደመሆኑ መጠን በምሥጢረ ጥምቀት ጸጋ ወደዚህ ከፍታ ወጥተናል። በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ከዚህ ከፍታ እንዳንወርድ እያሳሰበን እንዲህ ይላል፡-
“እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ” (ቆላ 3፡2- 4)።
ፍቅር በባሕርዩ ፍጥረትን ሁሉ ያስተሳሰራል። ፍቅር የቤተክርስቲያን እና የክርስቲያን ሁሉ ፍፁም መልክ ነው፤ በመሆኑም በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ ሁነኛ ተሐድሶ የሚረጋገጠው ምዕመናን ወደዚህ የቅድስት ሥላሴ የፍቅር ምሥጢር በቀረቡበት በጎነት ልክ ነው፤ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” (ቆላ 3፡14) እያለ ያበረታታናል። ፍቅር ኢየሱስ በልቤ ውስጥ ለሌላው የሚከፍተው የምሕረት በር እና የመጠበቂያ ከተማ ነው። በመሆኑም ከኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋ የተቀበልነው መዳን በግለሰብ ደረጃ የግል ንብረት አድርገን የምንጠብቀው ጉዳይ ሳይሆን፤ ይልቁንም ሌሎች ሁሉ ወደዚህ የጸጋ መዳን እንዲደርሱ ምልክት የሆንኩንንበት የጌታ መስቀል የሚታይ ምሥክርነት ነው። ስለዚህም ጌታ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትወር አይቻላትም!” (ማቴ 5፡14) እያለ የምልክትነታችንን ዐደራ ያስታውሰናል። በምሥጢረ ጥምቀት ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ባገኘው ሱታፌ “በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን” (2ኛ ቆሮ 2፡14)። መዓዛነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የሚፈልቅ በቤተ ክርስትያን ቅድስት ሥላሴያዊ ኅብረት ውስጥ የሚገለጥ የምሕረቱ ለዛ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስትያን በዚህ አይነት የምሕረት ለዛ እየተመላለሰ አንዱ ለሌላው የክርስቶስ የምሕረት ፊት ሆኖ እንዲያገለግለው ተጠርቷል። በዚህም ሰብዓዊ ግንኙነቶቻችን እየታደሱ እና በክርስቶስ እየዳኑ በሰላም እና በሁለንተናዊ ጨዋነት ስለሚገሩ “መንግሥትህ ትምጣ!” ለሚለው የጌታ ጸሎት የሚመጥን ኅብረት በመካከላችን እንዲያብብ ዕድል ያገኛል። በዚህም በእምነት አይኖች በባልንጀራዬ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ምሕረት እና ጥበብ የተገለጠበትን መለኮታዊውን ምስል በማስተዋል እና በማድነቅ ከቅዱስ ዳዊት ጋር “አፌ የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራል፤ ሥጋም ቅዱስ ስሙን ለዘላለም ከፍ ከፍ ያደርጋል” (ምዝ 145፡21) እያልኩኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ!
ይቀጥላል...
ሴሞ