ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Sunday, 20 March 2022 14:10
- Written by Super User
- Hits: 1175
- 20 Mar
ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት
ንባባት፡- ገላ 5፡ 1-26፣ ያዕ 5፡14-20፣ ሐዋ 3፡1-11
መዝሙር፡- አምላኩሰ ለአዳም
ስብከት፡- “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዓራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኲሎ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፤ እኔስ አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ” (መዝ 41፡3-4)።
ወንጌል፡- ዮሐ 5፡ 1-21
የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት ዘመጻጒዕ ተብሎ ይጠራል፤ ይህም የሕመሙማን ፈውስ ሰንበት፣ የመነካት ሰንበት፣ የነጻነት ሰንበት እና ከደዌ የመፈታት ሰንበት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዛሬው ክፍል ኢየሱስ ቤተ-ሳይዳ ወደምትባል አምስት መመላለሻዎች ወዳሏት መጠመቂያ ስፍራ እንደመጣ ይናገራል። ኢየሱስ ወደዚህ ሥፍራ መምጣቱ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ምሥጢር በትክክል የሚተረጉምልን ቁልፍ ተግባር ነው። ኢየሱስ ወደዚህ ስፍራ ሲመጣ “በበጎች በር” (ዮሐ 5፡2) በኩል እንደነበረ ቅዱስ ዮሐንስ ይናገራል። ይህ “በበጎች በር” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የብሉይ ኪዳን ካህናት በዚያ በር አጠገብ ለመሥዋዕት የሚቀርቡትን በጎች መርጠው፣ አጥበው የሚሸልቱበትን ሥፍራ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ወደዚህ በር መምጣቱ ወደሚታረድበት መንበረ ታቦት እና መሥዋዕት ለመሆን ወደሚዘጋጅበት መቅደስ መቅረቡን የሚያመላክት ነው።
ነገር ግን የእነዚህ በጎች ንጽህና እና መሥዋዕት ሆነው መቅረባቸው ለዓለም ሁሉ መዳን ሊያመጣ አልቻለም። ዓለም ከእነዚህ በጎች ደም ይልቅ በከበረ እና ንጹህ በሆነ ደም መታጠብ ነበረባት! መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን አውቆ ኖሮ ኢየሱስን ለዓለም ሲያስተዋውቀው “የዓለምን ኃጢአት የሚያጠፋ የእግዚአብሔር በግ እነሆ” (ዮሐ 1፡29) ይላል። በብሉይ ኪዳን ዘመን አብርሐም በልጁ ፈንታ ይሠዋው ዘንድ ቀንዶቹ በሐረግ የተያዘውን በግ እያስታወሰ በይስሐቅ ፈንታ የሚሰዋው እውነተኛ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ይመሰክርልናል። የሀገራችን ሥርዐተ አምልኮ ይህንን ተከትሎ የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ላይ በምናቀርበው ምልጣን “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሃጺባ በደመ ክርስቶስ” እያልን እንዘምራለን። ስለዚህ ኢየሱስ በበጎች በር አጠገብ ቆሞ መመልከታችን የእንስሳት ደም መሥዋዕት ማብቃቱን እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈሰው፣ ዓለምን ሁሉ የሚፈውሰው፣ ሰማይንና ምድርን አዲስ ያደርግ ዘንድ ምድር በአዲስ ልደት የምትታጠብበት የደም ጥምቀት የሚፈጸመበት ዘመን መምጣቱን የሚያሳይ ነው! በመሆኑም ምድር በእንስሳት ደም ሳይሆን በኢየሱስ ደም ታጥባ ፋሲካዋን ታከብራለች።
በመቀጠልም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ ሳይዳ የመጠመቂያ ስፍራ መኖሩን ይናገራል። በዚህም ሥፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መላእክት ወርደው ውኃውን እንደሚያናውጡት እና ውኃው ከዚህ የተነሳ የሚፈውስ ውኃ እንደሚሆን፣ ከመላእክቱ መውረድ የተነሳ የመለኮታዊ ፈውስ በውኃው ላይ እንደሚገለጥ እናነባለን። ነገር ግን የዚህ የቤተ ሳይዳ ውኃ ፈውስ፣ አቅም ላላቸው እና ሰው ላላቸው ለባለ ወገን ብቻ የሚሆን ውኃ ነበር። ኢየሱስ የቤተ ሳይዳውን ወኃ ሳይሆን በደሙ የሚቀድሰውን አዲስ ውኃ ይሰጥ ዘንድ በቤተ ሳይዳ መጠመቂ ሥፍራ ቆሟል። ጌታ ወደዚህ መጠመቂያ ሥፍራ መውረዱ አሁን መላእክት ሳይሆኑ የመላእክት ሁሉ ጌታ ራሱ ወደ ውኃው መውረዱን እና የአዲስ ኪዳን ውኃ የመከፈቱን የምሥራች የሚያበስር ነው። ይህም የምሥጢረ ጥምቀትን ጸጋ የሚያመላክት ሲሆን ኢየሱስ በዚያ መገለጡ እና ፈውስ ማድረጉ ምሥጢረ ጥምቀት ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተከፈተ የመለኮታዊ ምኅረት እና የዳግም ልደት ምሥጢር መሆኑን ያስገነዝበናል። የቤተ ሳይዳ ውኃ በመላእክት ኃይል የሥጋን ደዌ ሁሉ ይፈውስ እንደነበረ ሁሉ የአዲስ ኪዳን የጥምቀት ውኃ በኢየሱስ መለኮታዊ ሥልጣን እና በቅድስት ሥላሴ ስም ነፍስን እና ሥጋን ሁሉ ይቀድሳል፤ የአዲስ ኪዳን ውኃ እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴቶች ልጆች፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞችና እኅቶች፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ሆነን ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን የምንወለድበት የዳግም ልደት ምሥጢር አለው።
በቤተ ሳይዳ ውኃ ሕሙማን ከሥጋ ደዌ ተፈውሰዋል ነገር ግን እኛ በበለጠው በአዲስ ኪዳን ውኃ ከሥጋ ደዌ መፈወስ ሳይሆን ከቅድስት ሥላሴ ጋር የሥጋ ዝምድና አለን። እርሱ ስለወደደን በደሙ አጥቦናልና (ራዕ 1፡5) በዚህ ፍቅር መካከል ከእርሱ እና ከእኛ በስተቀር ንፋስ እንኳን ቢሆን መግቢያ የለውም፤ ምክኒያቱም በመካከላችን ያለው ቃልኪዳን ሥጋ ላይ በሚቀር ግርዛት ሳይሆን “ከሞቱ ጋር አንድ በሚያደርግ ጥምቀት ነው” (ሮሜ 6፡3)። ይህም ማለት ኃጢአት አንሰራም፣ አንወድቅም፣ አምላክን አናሳዝንም ማለት ሳይሆን ፍቅሩ ከእኛ ደካም ጋር የሚነጻጸር፣ ፍቅሩ በእኛ ዕለታዊ ማንነት ላይ የተመሰረት እና ተለዋዋጭ አይደለም ማለታችን ነው። እርሱ ካለብን ኃጢአት በላይ እኛን የሚያጸድቅበት ጸጋ፣ ከወረድንበት ሸለቆ በላይ እኛን ከፍ የሚያደርግበት ክብር፣ ከታሰርንበት ሰንሰለት በላይ አርነት የሚያወጣ ቃል፣ ከተበዘበዝንበት ቀንበር በላይ የጫንቃን ቁስል የሚፈውስ ዘይት፣ ከተዋረድንበት አጸያፊ ገጽታ በላይ አዲስ ካባ የሚያለብስበት አባታዊ ልብ አለው ማለታችን ነው። መጽሐፍ ይህንን ሲመሰክርልን እንዲህ ይላል፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናም፣ ዛሬም፣ እስከ ዘላለም ያው ነው!” (ዕብ 13፡8)/
ቅዱስ ዮሐንስ የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ አምስት በሮች እንደነበሩት ይናገራል። እነዚህ አምስት በሮች ወደ ፈዋሽ ውኃ የሚያስገቡ በሮች ናቸው። ሕሙማን በእነዚህ በሮች ወደ ፈውስ ይመጡ ዘንድ እነዚህ በሮች ተከፍተዋል፤ ነገር ግን በእነዚህ በሮች የሚገቡ ሁሉ ፈውስ ያገኛሉ ማለት አይደለም። በበሮቹ ቢገቡም ወደ ፈዋሽ ውኃው የሚያስገባቸው ወገን ያስፈልጋቸው ነበር። ነገር ግን በእነዚህ በሮች እንገባ እና ወደ ፈዋሽ ውኃ እንደርስ ዘንድ በሮቹ የት አሉ? ዛሬስ የፈውስ በሮች ክፍት ሆነው የሚታዩት የት ነው? ነቢዩ ኢሳያስ ከዘመናት በፊት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ 53፡5) ይላል። ስለዚህ እነዚህ አምስቱ የቤተ ሳይዳ የፈውስ በሮች አምስቱ የጌታ ቁስሎች ናቸው። እነርሱ በምስማር እና በጦር ከመከፈታቸው አስቀድሞ በእርግጥ ከዘላለም ጀምሮ በፍቅር ኃይል ተክፍተው ነበርና ጌታ “በሩ እኔ ነኝ” (ዮሐ 10፡9) ይላል፤ በእርሱ በኩል እንድንገባ እና እንድንወጣ ብሎም መሰማርያ እንድናገኝ ይጋብዘናል። በእነዚህ በሮች በኩል ወደማይታየው አምላክ መመልከት እንችላለንና ጌታ “እጆቼን እና እግሮቼን እዩ!” (ሉቃ 24፡39) እያለ ወደ ቅድስት ሥላሴ ልብ ትርታ የሚያሳየንን የምኅረት በር ይጠቁመናል። በእርግጥም ዐቢይ ጾም በመስቀል መንገድ የጌታን ቁስሎች የምናስተነትንበት ጉዞ ነው።
ቅዱስ አውጉስጢኖስ እነዚህን የቤተ ሳይዳ በሮች በሚመለከት እነርሱ አምስቱ የሙሴ የሕግ መጽሐፍት ምልክቶች ናቸው ይላል። በመሆኑም አይሁድ በሕግ እንጂ በጸጋ አልነበሩምና ሕግ የነፍስን ቁስሎች ለመፈወስ ስልጣን የለውም። በዚህም በቅዱስ ዮሐንስን የወንጌል ዕውሮች፣ አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ እየተባሉ በስም የተጠቀሱ የበሽታ አይነቶች ሁሉ ውጫዊ እና አካላዊ ጎዶሎነትን የሚያሳዩ በመሆናቸው ሕግ ሁሉን ሊፈውስ እንደማይቻለው እና ሁሉን እንደማይጠቀልል የሚያመላክት መሆኑን ይገልጻል። የዕብራውያን መጽሐፍ ስለዚህ ሲመሰክር “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና” (ዕብ 10፡4) እያለ አዲሱ ደም የግድ እንደሆነ ያሳየናል። እነዚህን በቤተ ሳይዳ የወደቁ ሕሙማንን ማንሳት እና ሕይወት መዝራት የሚችለው የኢየሱስ ደም ብቻ ነው። ደሙ ያነሳል፣ ደሙ ያጥባል፣ ደሙ ያነጻል፣ ደሙ ይቀድሳል፣ ደሙ ያከብራል፤ ደሙ ዘማዊውን ድንግል ያደርጋል።
እነዚህ ሕሙማን በዮሐንስ ወንጌል የተገለጹበት ሁኔታ ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። በመጀመርያ ሕመማኑ “በመሬት ላይ ተኝተው” ነበር የሚለው ስዕላዊ አገላለጽ ኃጢአት በነፍስ ላይ የሚያደርሰውን ቁስል የሚያመለክት ሲሆን፣ ነፍስ በኃጢአት ቀንበር ወደ መሬት ተደፍታ፣ በምድራዊ ነገሮች ተገዝታ እና ተበዝብዛ መድከሟን መመልከት እንችላለን። እንዲህ ያለችው ነፍስ ወደ እግዚአብሔር ቀና ማለት የምትችልበትን የጸጋ ኃይል ስለተነጠቀች ወደ ውኃው የሚጥላትን ሰው ከመጠባበቅ የተለየ ሌላ ተስፋ የላትምና ጌታ በቀረባት ጊዜ “ጌታ ሆይ ሰው የለኝም!” (ዮሐ 5፡7) እያለች ተስፋዋ ሁሉ እንደተሟጠጠ ትናገራለች። ሰው የለኝም! ምሥጢሬን የማሳየው፣ በምሥጢሬ የምታመንበት፣ ቁስሌን የማሳየው፣ በቁስሌ መክፋት የማይጠየፈኝ፣ የማለቅስበት፣ የዕንባዬን ዋጋ እና የተስፋ መቁረጤን ጥግ የሚያውቅልኝ ሰው የለኝም! ለተወሰነ ጊዜ የሕይወታችንን ጉዞ ብናስተውለው ይህ “ሰው የለኝም!” የሚለው የቤተ ሳይዳው ሰው ዋይታ የእያንዳንዳችን መሆኑን መመልከት እንችላለን።
ዛሬ ቁስላችንን፣ የምናፍርባቸው የሕይወት ገጠመኞቻችንን፣ የወደቅንባቸው፣ የተማረክንባቸው ኃጢያቶቻችንን የምናዋየው ሰው ማነው? ለማን ነው ልባችንን አምነን መክፈት የምንችለው? ለራሳችን እንኳን ልናስበው ሰላም የሚነሳንን እና የሚያሸማቅቀንን ነገር አውጥተን የምንነግረው ሰው ይኖረን ይሆን? ወይስ ከቤተ ሳይዳው ሰው ዋይታ ተውሰን እኛም “ጌታ ሆይ ሰው የለኝም!” እንላለን? ነገር ግን አዲስ ኪዳን የሚያጽናና መለኮታዊ የምሥራች አለው፤ ይኸውም ሰው እንደሌለን የሚያወቅ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች መቅበዝበዛችንን (ማቴ 9፡36፤ ማር 6፡34) ያየው ኢየሱስ ይህንን አውቆ ሰው ለሆንልን ሰው ሆኗል! ስለዚህ ወደ እኔ ቀርቦ “መዳን ትወዳለህን” (ዮሐ 5፡7) እያለ እጁን ይዘረጋልኛል።
እርሱ የእኔን የተዋረደ ሥጋ ገንዘቡ አድርጎ “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሰን አዋረደ” (ፊል 2፡7-8) ስለዚህ ከዚህ በላይ የሚያጸይፈው፣ ከእኔ የሚያሸሸው፣ የቁስሌ ሽታ የማያስጠጋው ኃጢአት የለም። ስለዚህ ጌታ ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል፤ ወደ ወረድንበት ሸለቆ ጥግ፣ ወደ ተያዝንበት የአለት ንቃቃት ስር፣ የአሳማ ምግብ እስከ መጎምጀት ክብራችንን ወደተገፈፍንበት ባርነትና ኃጢአት ይመጣል! እርሱ ለእያንዳንዳቸን ሊያደርግ የሚፈልገውን ነገር ነቢዩ ኤርሚያስ ሲናገር “በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፡-ቀንበርህን ከአንገት እሰብራለሁ፤ እሥራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም” (ኤር 30፡8) እያለ ተስፋ ይሰጠናል።
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ትረካውን ቀጥሎ በቤተ ሳይዳ የመጠመቂያ ሥፍራ የነበሩትን ሰዎች ሁኔታ እያብራራ፣ አንደኛ ከሕሙማኑ መካከል ገሚሱ “ሰውነታቸው የሰለለ” እንደነበር ይናገራል። ይህ የዮሐንስ አገላለጽ በፍትወት ኃጢአት የምትሰቃይ ነፍስ ያላትን አካላዊ ገጽታ የሚያመለክት ሲሆን ሥጋ ከፍትወቱ እና እርሱንም ከሚያሟላበት ነገር ውጭ ሌላ ምንም ነገር ማድረግ በማይችልበት፣ የነፍስ ኃይላት በዚህ ያልተገራ ሥጋዊ ፍትወት የተጠመዱበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ንጽሕና ሲጎድል የሰውነት ሰው ሆኖ በምልዐት የመገለጥ ኃይል ይጎድላል፤ ንጽሕና የጉልምስናን ዘመን እንደ ንሥር ወጣት አድርጎ ያድሳል። በመቀጠልም በሁለተኛ ደረጃ ዕውራን በዚያ እንደነበሩ ዮሐንስ ይናገራል። ዮሐንስ ዕውራን የሚላቸው ማየት የተሳናቸውን፣ ውጫዊ የሆነ አካላዊ የማየት አቅም የሌላቸውን ብቻ ሳይሆን ያልተገራ ፍትወት የሚሰለጥንበትን አዕምሮ ጭምር ነው። መጽሐፈ ጥበብ 2፡21 “ምክኒያቱም እነርሱ እንደዚህ አሰቡ በዚህም ሳቱ፤ ጥላቻቸው አሳውሯቸዋል” እያለ ዕውርነት ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳተምረናል። ዕውርነት የነፍስ የማስተዋል ብርኀን መደብዘዝ ነው። ሰውነቱ የሰለለ እና የታወረ ሰው ጸንቶ መቆም ስለማይችል እና ጸንቶ የሚቆምበት ቅጥር እና መልህቅ ሰለሌለው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህንን የሰው ልጅ ሁኔታ “ሽባነት” እያለ ይገልጸዋል።
በዚህ የወንጌል ክፍል የምናስተውለው የሕሙማኑ ሁኔታ ለመንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ቁም ነገር ያስተምረናል፤ ቅዱስ ዮሐንስ የሕሙማኑን ሁኔታ ሲገለጽልን “የውኃውን መናወጥ የሚጠባበቁ” ነበሩ ይላል። ፈውስን መናፈቅ እና ፈውስን መጠበቅ ለመዳን ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ የሚጠይቅ ተግባር ነው። መጠበቅ እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን ይጠይቃል። ዛሬ የምንገኝበት የዐቢይ ጾም ወቅት የጸጋ ወቅት ነው፤ የመሢሁን ሕማም እና ሞት በእውነት እና በመንፈስ እየተካፈልን ፈውስ ሁሉ የሚገኝበትን ትንሳኤውን የምንጠባበቅበት የጸጋ ዘመን፣ የተወደደው የጌታ ዓመት ዛሬ ነው። ትልቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ መቁረጥ ነው! ስለዚህ ውኃውን ሳይሆን ደሙን በተስፋ እየጠበቅን ደግሞም በመካከላችን በምሥጢረ ቊርባን የደሙን ዋጋ እያከበርን፣ እርሱን እንመስል ዘንድ ከሥጋው እየበላን እና ከደሙ እየጠጣን እንጠብቅ! ከእምነት አባታችን ከያዕቆብ ጋር እግዚአብሔርን በእምነት እየታገልን እና ካልባረከኝ አልለቅህም እያልን መድኃኒትን እንጠብቅ!
ነገር ግን እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ሌላ ቁም ነገር አለ። የቤተ ሳይዳው ሰው ጌታ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የሚያስደንቅ ምላሽ ነው፤ ጌታ “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ሰላሳ ስምንት ዓመት በዚያ ሁኔታ ሲሰቃይ የነበረው ሰው “ጌታ ሆይ ወደ ውኃው የሚጥለኝ ሰው የለኝም!” እያለ የራሱን የመዳን መርሐ ግብር ለጌታ ይናገራል። ምናልባት የዚህ ሰው ታሪክ ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሰን ለምጽ የመታውን ታላቁን የሶርያ ንጉሥ ንዕማንን እንድናስታውስ ይጋብዘናል። ንዕማን ፈውስ ፍለጋ ሀገር አቋርጦ ወደ ነብዩ ኤልሳዕ ሲመጣ ከለምጹ ይፈወስ ዘንድ ነቢዩ ኤልሳዕ በዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ እንዲታጠብ በነገረው ጊዜ “ንዕማን ግን ተቆጥቶ ሄደ፤ እንዲህም አለ፡- እነሆ ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ የለምጹንም ሥፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር!። የደማስቆ ወንዞች አባርናና ፋርፋ ከእሥራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱም ውስጥ መታጠብ እና መንጻት አይቻለኝም ኖሯልን?” (2ኛ ነገ 5፡11-12) ንዕማን ፈውስ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚፈወስ ጭምር የራሱ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። ይህ አይነቱ ለራስ መድኃኔዓለም የመሆን ፍላጎት በእግዚአብሔር ዘንድ ሥፍራ የለውም። ዐቢይ ጾም የመሰራት፣ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የመፈወስ እና እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ፣ በእግዚአብሔር ሐሳብ፣ ለእግዚአብሔር ሐሳብ የመለወጥ ጉዞ ነው። ዛሬ ጌታ መዳን ትወዳለህን? በሎ ለሚያቀርብልን ጥያቄ ከእመቤታችን ትህትና እና እምነት ጋር ተባብረን “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ እንዳንተ ፈቃድ ይሁንልኝ!” የምንልበት የጾም ወቅት ይሁንልን!
ሴሞ