እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የጌታ ልደት ለሰላም ነው!

የጌታ ልደት ለሰላም ነው!

Rየጌታን መምጣት በምንጠባበቅበት የዝግጅት ጊዜ መጽሐፈ ጥበብ ስለ ትስብዕቱ ምሥጢር ሲናገር በቅድስት ሥላሴ መካከል ስለነበረው ተግባቦት እንድናሰልሰል ይጋብዘናል፡-

“ሰላማዊ ጸጥታ በሁሉ ላይ በሰፈነ ጊዜ፣ ሌት ከተጋመሰች በኋላ ኃያሉ ቃልህ ከንጉሣዊው ዙፋን እንዳትጠፋ በተፈረደባት መሬት እምብርት ላይ እንደ ጨካኝ ጦረኛ ከሰማይ ዘሎ ወረደ” (ጥበብ 18፡14-15)

እነዚህ ቃላት የትስብዕቱን ምሥጢር የሚናገሩ ቃላት ናቸው፤ ቃል ከእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ ፍጹም አርምሞ ውስጥ እንዴት ባለ ኃይል እንደወጣ እና እንደተገለጠ እንድንመለከት ዕድል ይሰጡናል። ፍጹም በሆነ ዘላለማዊ አርምሞ ውስጥ የሚኖረው እግዚአብሔር አብ በሁሉም ነገር ላይ፣ በሰማይም ይሁን በምድር ስለ ሁሉም ነገር የተናገረው ዘላለማዊ ቃል ጸጋ እና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን ያደረው አንድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

በአርምሞ ውስጥ ታላላቅ ነገሮች ይከናወናሉ፤ በሁካታ መካከል ያለው ግን ከላይ ከላይ የሚታየው ትርፉ ነገር ብቻ እንጂ በጥልቅ ጸጥታ ውስጥ ያለው ነገር አይታይም፤ በውስጣዊ ሰላም በተሞላ ዐይን የሚታየው፤ ለማያዳግም ውሳኔ በሚያዘጋጅ አርምሞ ውስጥ ያለው ነገር ድምጽ ሳያሰማ ይገለጣል። መገለጡንም የሚቋቋም አይኖርም። ልብ እንዲህ ባለው መገለጥ በፍቅር ሲዳሰስ ነፍስ ከፍ ወዳለ ነጻነት ደርሳ በውስጧ እንዲህ ያለው መገለጥ ለሚያፈራው ፍሬ የተዘጋጀች የእግዚአብሔር የወይን እርሻ ትሆናለች። በሀገራችን አባባል “ዝም ያለውን ፍራ” እንደሚባለው በጥልቅ ጸጥታ ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት እጅግ ኃይለኛ ናቸው፤ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ልደት፣ ሞት፣ ወ.ዘ.ተ. በጸጥታ የሚከናወኑ ነገሮች በመሆናቸው የበረቱ የሰው ልጅ ሕይወት ቁም ነገሮች ናቸው።

በመለኮታዊ አርምሞ ውስጥ ተሰውሮ የነበረው ቃል “ጊዜው በደረሰ ጊዜ” (ገላ 4፡4) ጸጋ እና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን ተገልጧል። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በመጀመርያ ቃል ነበረ” ካለ በኋላ ይህ ቃል የት እንደነበረ ሲናገር “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ይላል፤ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል ሰማይ እና ምድር የተዘረጉበት ጥበብ፣ እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ መልካም አድርጎ ያበጀበት ቀመር፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ የቆመበት ምሦሦ እና ሕይወት ያለው ፍትጥረት ሁሉ ሕልውናውን ያገኘበት የመጨረሻው የፍጥረት ሕልውና ጥግ ነው፤ በመሆኑም ቅዱስ ዮሐንስ “ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም” (ዮሐ 1፡3) በማለት ይመሰክርለታል።

ይህ ዓለምን እና ሞላዋን ሁሉ ፈጥር ካበቃ በኋላ በነገሮች ፍሰት ውስጥ ጣልቃ በማይገባ  መለኮታዊ ጨዋነት ዓለም በራስዋ ዑደት እንድትንቀሳቀስ በመለኮታዊ ትህትናው ለፍጥረት ሁሉ ነጻነቱን ያጎናጸፈው አምላክ፣ የነገሮች ሁሉ የመጨረሻው ምንጭ፣ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር፣ ማንም የማያንቀሳቅሰው፣ ነገር ነገር ግን እርሱ የሁሉ ነገር ዘዋሪ፣ በዓለም ውሱንነት ሊያዝ እና ሊለካ የማይችል፣ ስለ እርሱ ከምናውቀው ይልቅ የማናውቀው ጥልቀቱ ከአእምሮ በላይ የሆነ፣ ስለ እርሱ የምንናገረው እርሱን ከሚመስለው ይልቅ የማይመስለው የሚበልጥ ሆኖ ሳለ፣ ስለ እርሱ እንናገር እና ስለ እርሱ እንመሰክር ዘንድ ከዘላለም ጅምሮ ተሰውሮ የኖረው መለኮታዊ ክብር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በመካከላችን ተገልጧል።

ይህ መገለጥ በመለኮታዊ አርምሞ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ፍቅር እንድናስተውል ይጋብዘናል። የጌታ መገለጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ሥጋ ለብሶ በእያንዳንዳችን ውስጥ የመግባቱ እውነታ ነው፤ በመሆኑም ይህ ከሰማያት የወረደው እና በመካከላችን የተገለጠው ቃል የመለኮታዊ ፍቅር እንቅስቃሴ ምሥክር ነው። “ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከሰማያት ስቦ እስከሞት አደረሰው” የሚለው የመሥዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የዚህ መለኮታዊ ፍቅር እንቅስቃሴ በቅድስት ሥላሴ መካከል ብቻ ያለ ቁም ነገር ሳይሆን ወደፍጥረት ሁሉ የሚፈስ እና ፍጥረትን ሁሉ የሚያጸና፣ የሚያጽናና እና የሚቀድስ የፍቅር እቶን መሆኑን ያመለክታል። ይህ ፍቅር በሰው አእምሮ ልንረዳው የማይቻለን የራሱ አመክንዮ እና የራሱ ዓላማ ያለው፣ ለሚቀበሉት ሁሉ ራሱን የሚገልጥ እና የእግዚአብሔር ልጅነትን ክብር የሚያጎናጽፍ መለኮታዊ ሥጦታ ነው።

ይህ መለኮታዊ ሥጦታ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ክብር እንደመሆኑ መጠን አምነው ለሚቀበሉት ሁሉ ሁለንተናዊ ሰላምን የሚያጎናጽፍ የአዲስ ሕይወት ጥሪ ነው። ይህ አዲስ ሕይወት ከህጻኑ ኢየሱስ ጋር አብሮ እያደገ እና ይበልጥ እርሱን እየመሰለ የሚያብብ ሕይወት በመሆኑ የኢየሱስ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይወርሳል። ኢየሱስ በተወለደበት ቅጽበት ለምድር ሁሉ የመጣው መልእክት “ሰላም ይሁን” የሚል መልእክት ነው። ይህ የሰላም ጥሪ እያንዳንዳችን የሰላም ሐዋርያ እንሆን ዘንድ የሰላም አለቃ ተብሎ በተጠራው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የማስታረቅን አገልግሎት ተቀብለናል። ይህ የማስታረቅ አገልግሎት በጸሎት ሕይወት የሚገለጥ፣ መጸለይ ለማይችሉት ጭምር በእነርሱ ፈንታ በክርስቶስ ኢየሱስ ስም በእግዚአብሔር አብ ፊት ቆመን በመንፈስ ቅዱስ ልሳን የምንቃትትበት ሁነኛ አገልግሎት ነው።

ጸሎታችን “ሰላም ይሁን” ተብሎ ለተበሰረው የምሥራች ተግባራዊነት የምንንቀሳቀስበት መንፈሳዊ ኃይል ነው። ሰላም የሚለው ቃል ሰው የመሆን ሁሉ ፍጻሜ እና ምልዓት ነው፤ ይህም ሰላም ፖለቲካዊ መረጋጋት ወይም ማኅበረሰባዊ የተሳለጠ ኑሮ እና ተግባቦት ማለት ሳይሆን፣ ይልቁንም ሰላም ሰው የመሆን ትርጓሜ ነው። የሰው ልጅ የፍጥረት ሁሉ የሰላም ባለዐደራ እና የሰላም አምባሳደር ነው። ሰላምን የፖለቲካ፣ የፍትሐዊ ምጣኔ ኃብት ወይም የኅብረተሰባዊ ኑሮ መሳለጥ ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ የሰውን ልጅ ዋጋ በእጅጉ ማሳነስ ነው። ሰላም ከዚህ ባሻገር የሚመለከት እና የሰውን ልጅ በሁለንተናው የሚቀድሰው የስብዕናው ክብር ነው።

 መጽሐፍ ቅዱስ ሰላም ብሎ የሚጠራው የሰውን ልጅ ምድራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም እግዚአብሔርን በማዳኑ እና በፍቅሩ ወደ እያንዳንዳችን ዘንበል ያለበትን መለኮታዊ ትህትና ነው፤ እግዚአብሔር በማዳኑ እና በፍቅሩ ወደ እኛ ዘንበል ያለበት ትህትና፣ ጸጋ እና እውነት ተሞልቶ በመካከላችን ያደረው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ስለዚህ ሰላም በመጀመርያ ደረጃ በጎ ጽንሰ ሐሳብ ሳይሆን ሰላም እውነት መንገድ እና እውነት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።  በመሆኑም ያለ መጠን ተሰፍሮ የተሰጠን ይህ መለኮታዊ ጸጋ ከየትኛውም ድንበር ክፍ ብሎ ከሞት በበረታ ፍቅር ራሱን ለእያንዳንዳችን በመስቀል ላይ አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ወድዶናልና ከዚህ የመስቀል መሥዋዕት ዋጋ በታች በሆነ በሌላ ምንም ነገር እንዳንገዛ እርሱ ራሱ የከበረ ዋጋችን ሆኗል።

በዚህም ምክኒያት ሰላም የፍጥረትን ደህንነት በመጠበቅ፣ በታሪካችን ትርጉም ውስጥ ለተቀበልነው የመዳን ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት እና በመጨረሻም በሰማያት በምናገኘው የሰላም ምልዓት ተስፋ በመጽናናት እና በመጽናት የምንመላለስበት የአዲስ ሕይወት ጎዳና ነው። በዚህ ውስጥ ፍጥረት፣ የእያንዳንዳችን የሕይወት ታሪክ እና ምልዓት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ይስተዋላሉ። በጌታ ልደት የታየው የእግዚአብሔር መገለጥ የተከናወነው በዚህ አይነት ነው። እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፍጥረት መካከል፣ በታሪካችን ውስጥ ተገልጦ ወደ ተስፋ ፍጻሜ እንደርስ ድረስ መንገዱን ከፍቶልናል።

ሻሎም שָׁלוֹם የሚለው የእብራይስጡ ቃል ጽንሰ ሐሳብ ሰላም ፣ ስምምነት ፣ ሙሉነት ፣ ሙላት ፣ ብልጽግና ፣ ደህንነት እና መረጋጋት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን እና ሞላዋን ከፈጠረ በኋላ ያረፈባት ዕለት የዚህ ሰላም ትርጓሜ በመሆኗ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ያደርግ ዘንድ የተፈጥሮን ዑደት በሚያከብር የጊዜ ቀመር መንቀሳቀስ እና የፍጥረትን ሁለንተናዊ ሰላም መጠበቅ ይገባዋል። የሰው ልጅ የፍጥረትን ሁለንተናዊ ቅድስና ችላ ባለበት የሕይወት ክፍል ሁሉ ግጭት እና ጦርነት፣ ኃጢአት እና ዕዳ እንዲሁም ኢፍትሐዊነት በሰው ልጆች መካከል ቤታቸውን ሰርተው ይቀመጣሉ።

የሰው ልጅ ለሕይወቱ ትርጉም እና ፈውስ ያገኘበትን የእግዚአብሔርን የጸጋ ጉብኝት ተቀብሎ ለእርሱ በሚሰጠው ተግባራዊ ምላሽ ወደ ሰላም ወደብ መድረስ ይችላል። ሰላም በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የመለኮታዊ ጸጋ ምልዓት መገለጥ በመሆኑ በውስጡ ሁለንተናዊ መቀደስን እና ፍቅርን ይዟል። እያንዳንዳችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የመልበስ ምሥጢር በኩል እንዲህ ወዳለው ሰላም እና በረከት ቀርበናል።  በዚህ የጸጋ ጉብኝት የተጠመቀ ክርስትያን የሕይወቱን አቅጣጫ ወደዚህ በረከት ፍጻሜ በማድረግ ዕለት በዕለት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ተስፋው ፍጻሜ እየቀረበ ያድጋል። በዚህ አይነት እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ በኩል ከእያንዳንዳችን ጋር የሰላም ቃልኪዳን ያደርግ ዘንድ ወደዚህ ሰላም ይጋብዘናል። ይህ ሰላም በጠረጴዛ ዙርያ የሚደረስበት የጋራ ስምምነት እና የወል ተግባቦት ማሰርያ ሳይሆን ይልቁንም ይህ ሰላም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ስለዚህም “ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል”  (ኢሳ 9፡6)።

ይህንን የሰላም አምላክ ለመቀበል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ህጻኑን ከነመስቀሉ ይቀበል ዘንድ ልቡን ሊከፍት ይገባዋል። የሰላም ዕጦት የልብ መዘጋት እንጂ የጦር መሳርያ መትረፍረፍ አይደለም። ሰው ሰውን የሚገድለው በልቡ ነው፤ የሰው ልጅ ወንድሙን ማፍቀር ባቆመበት ቅጽበት ያ ሰው በልቡ ውስጥ ሞቷል፤ በዚያ ሰው ላይ የሚያደርሰው ሌላው ጉዳት ሁሉ አስቀድሞ በልቡ በገደለው ላይ የሚሰነዝረው የፈሪ ዱላ እንጂ ሌላ አዲስ ጦርነት አይደለም። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተደረገው እና የሆነው ይህ ነው፤ አስቀድመው በልባቸው ፈጽመው ጠሉት፤ ስለዚህም ግርፋቱ የጥላቻቸውን ወሰን ስላላረካላቸው ሞቶ እስኪያርፉ እና ጥላቻቸው ስኪረካ ድረስ ወደ መስቀል አቻኮሉት! እርሱ ግን በመስቀል ላይ እንኳን ሆኖ “ተጠማሁ!” ይላል። ዛሬም ፍቅርን ፍለጋ ይጣራል!

 እግዚአብሔር አምላክ ፍቅር ባልነበረበት ስፍራ ፍቅርን እንዳደረገ እንዲሁ እኛም ፍቅር ባልሆነበት ስፍራ ፍቅር ሕልውናውን መልሶ ያገኝ ዘንድ ተጠርተናል። እንደ ፍቅር ሥጦታ በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንደመታመን ያለ በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል ሥጦታ የለም፤ ዛሬም ከጌታ ጋር በአንድ ድምጽ “ተጠማሁ!” የሚል የሰው ዘር ባለበት የጌታን ልደት ስናከብር ፍቅርን ከማክበራችን አስቀድመን ፍቅርን እንድንሰጥ፣ በልባችን ያሉትን ሙታን በፍቅር ቃል እንድናነቃቸው እንጋበዛለን።

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት